“አረመኔዋ ሩሲያ አትታመንም” - ዜለንስኪ
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ አለምን “ለመጨረሻው ጦርነት እየገፋች ነው” ብለዋል
ኢራን በበኩሏ አሜሪካ ጦርነቱን እያጋጋለች ነው ስትል ወቅሳለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ሩሲያን “የማትታመን አረመኔ” ሲሉ ገልጸዋታል።
ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ ከምግብ እስከ ነዳጅ የትኛውንም ነገር እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች መሆኑን ነው ያነሱት።
ሩሲያ ለመላው አለም ስጋት መደቀኗን ባብራሩበት ንግግራቸው ኒዩክሌር የታጠቀችው ሞስኮ “አለምን ለመጨረሻው ጦርነት እየገፋች ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን የመጠቀም መብት የላትም ያሉት ዜለንስኪ፥ የጦር ወንጀሎች እንዲቆሙና በወረራ የተያዙ ስፍራዎችም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
ወደ ሩሲያ የተጋዙ ዩክሬናውያን እንዲመለሱና የጠየቁት ፕሬዝዳንቱ፥ ሩሲያን በ”ዘር ጭፍጨፋ” ከሰዋል።
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ሩሲያ ዩክሬናውያን ህጻናትን አስገድዳ አስገብታለች በሚል በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።
ሩሲያ ግን በኬቭም ሆነ በአይሲሲ የሚቀርቡ ክሶችን ሀሰት ነው በሚል ስታጣጥል የቆየች ሲሆን፥ ፕሬዝዳንት ፑቲንም በአለማቀፍ መድረኮች መሳተፍ ካቆሙ ወራት ተቆጥረዋል።
በ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ይሳተፋሉ ተብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በኒውዮርኩ ንግግራቸው ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር በድብቅ የሚካሄድ ድርድርን አንቀበልም ብለዋል።
የጦርነቱ ዳፋ ለመላው አለም እንደሚተርፍ በመጥቀስም የድጋፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ አቻቸው “የሩሲያ የዩክሬን ወረራ ካልቆመ የከፋ ችግር ይፈጠራል” በሚል በትናንትናው እለት ያደረጉትን ንግግርም አድንቀዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በበኩላቸው አሜሪካ የዩክሬኑን ጦርነት እያጋጋለች ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
“አሜሪካ በዩክሬን ጦርነት በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈች ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ራይሲ፥ የዚህ መዳረሻውም የአውሮፓ ሀገራትን ማዳከም ስለመሆኑ በ78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል።
ቴህራን ለሞስኮ ድሮኖችን መሸጧን የሚጠቅሰው የሬውተርስ ዘገባ፥ የፕሬዝዳንት ራይሲ ንግግርም ይህንኑ አጋርነት ያሳየ ስለመሆኑ አብራርቷል።