ወታደራዊ ረቂቅ ህግ በእስራኤል መንግስት ውስጥ ክፍፍል ፈጠረ
አክራሪ የአሁድ ኦርቶዶክሶች ለውትድርና እንዳይመለመሉ የሚያስችላቸው ልዩ መብት በሀገሪቱ ዜጎች መካከል የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል
የእሰራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዩአቭ ጋላንት ረቂቅ ህጉ በነገው እለት ለካቢኔ እንደሚቀርብ እና እሳቸው ግን እንደማይደግፉት ተናግረዋል
ወታደራዊ ረቂቅ ህግ በእስራኤል መንግስት ውስጥ ክፍፍል ፈጥሯል።
አንድ የእስራኤል ጦር ካቢኔ አባል አክራሪ የአይሁድ ኦርቶዶክሶች ለጦርነት እንዳይመለመሉ የቀረበው ረቂቅ ህግ የሚጸድቅ ከሆነ በብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስት ውስጥ ያላቸውን ኃላፊነት አንደሚያቆሙ ተናግረዋል።
"ሀገሪቱ ይህን አትቀበለውም፣ ረቂቅ ህጉ በክንሰት(ፖርላማ) የሚጸድቅ ከሆነ እኔ እና ባልደረቦቼ ከብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱ ራሳችንን እናገላለን" ብለዋል የአማካኝ ፖለቲከኛው ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ።
በቅርቡ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት መሰረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የበለጠ ተቀባይነት ያላቸው እና የቀድሞው ወታደራዊ አዛዥ ቤኒ ጋንዝ የአንድነት መንግስቱ ከሀማስ ጋር የሚያካሂደው ጦርነት እንዴት መመራት እንዳለበት ድጋፍ አድርገዋል።
ጋንዝ "በመንግስት የቀረበው የምልመላ ህግ በአንድነት ሆነን ጠላትን መዋጋት ባለብን ወቅት ክፍፍል ሊፈጥር የሚለችል ከባድ የሞራል ውድቀት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የጋንዝ ፓርቲ ብቻውን የኔታንያሁን መንግስት መጣል አይችልም። ነገርግን የመከላከያ ሚኒስትሩ ይህን ረቂቅ ህግ መቃወማቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ፓርቲ ልኩድ ውስጥም ክፍፍል መኖሩን የሚጠቁም ነው ተብሏል።
የረቂቅ ህጉ ይዘት ይፋ አልሆነም፣ ነገርግን ለእስራኤል መገናኛ ቡዙኻን ሾልኮ ከወጣው የረቂቅ ህጉ የተወሰነ ክፍል መረዳት እንደሚቻለው አከራካሪ የነበረውን አክራሪ የአይሁድ ኦርቶዶክሶች ለውትድርና እንዳይመለመሉ የሚያደርገውን ልዩ መብት የተመለከተ ነው።
በአሜሪካ ይፋዊ ጉብኝት እያካሄዱ ያሉት የእሰራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዩአቭ ጋላንት ረቂቅ ህጉ በነገው እለት ለካቢኔ እንደሚቀርብ እና እሳቸው ግን እንደማይደግፉት ተናግረዋል።
ረቂቅ ህጉ ለፓርላማ የሚቀርበው ካቢኔው ካጸደቀው በኋላ ነው።
አክራሪ የአሁድ ኦርቶዶክሶች ለውትድርና እንዳይመለመሉ የሚያስችላቸው ልዩ መብት በሀገሪቱ ዜጎች መካከል የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
13 በመቶ የሚሆነውን የእስራኤል ህዝብ የሚወክሉት የአክራሪ ኦርቶዶክስ ፓርቲዎች በኔታኔያሁ ለሚመራው መንግስት ድጋፋቸውን በመቸር ይታወቃሉ። በዚህ ምትክ የሚወክሉት ህዝብ በዩኒፎርም ከማገልገል ይልቅ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲያጠና ይፈልጋሉ።