የአዘርባጃን እና አርሜኒያን አሁን ተኩስ አቁም ላይ ናቸው
በናጎርኖ ካራባህ አካባቢ ምክንያት ጦርነት ላይ የነበሩት የአዘርባጃን እና አርሜኒያን መሪዎች ፊት ለፊት ሊገናኙ መሆኑን የአውሮፓ ሕብረት አስታወቀ፡፡
የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊየቭ እና የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሽንያን ከአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ሊቀመንበር ሚሼል ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ከስምምነት ላይ ደረሰዋል ተብሏል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በብራሰልስ ተገናኝተው እንደሚመክሩ የገለጸው ሕብረቱ ሁለቱም ለመገናኘት መስማመታቸው ተገልጿል፡፡ በምክክሩም ሀገራቱ እንዴት ወደዚህ ጦርነት እንደገቡ ውይይት እንደሚደረግም ነው የተገለጸው፡፡
የአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሼል ቃል አቀባይ ሁለቱ መሪዎች በቀጣናዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የምስራቅ እና ምዕራብ አውሮፓ ድንበር አካባቢ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ መሪዎቹ በቤልጄም ብራሰልስ የሚገናኙት በፈረንጆቹ ታህሳስ 15 ቀን 2021 እንደሆነም ሕብረቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ሁለቱን ሀገራት ለዚህ የከፋ ጦርነት ያደረሳቸው ናጎርኖ ካራባህ የሚባለው ክልል ሲሆን ይህ ክልል በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዘርባጃን ቢሆንም የክልሉ ነዋሪዎች የአርመን ብሔር ተወላጆች ናቸው፡፡
የናጎርኖ ካራባህ ነዋሪዎች በአዘርባጃን ሥር መሆናቸውን ካለመፈለጋቸውም በላይ ራስ ገዝ አስተዳደርን መመስረት ይፈልጋሉ፡፡ በመሆኑም ነዋሪዎቹ የሚወግኑት ለአርሜኒያ ጋር ነው። እነርሱም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚደገፉትም በአርሜኒያ መንግሥት እንደሆነ ነው የሚገለጸው።
ሁለቱም መሪዎች በመከላከያ ሚኒስትሮች በኩል ቀጥታ ግንኙነት እንዲኖር ስምምነት አድርገዋልተብሏል፡፡ ይህም ግጭቱን የማስቆም አንድ አካል መሆኑ ተገልጿል፡፡ አውሮፓ ሕብረትም ሁለቱም ወገኖች ተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ አሳስቧል፡፡ ሩሲያ፤ አዘርባጃን እና አርሜኒያ ተኩስ እንዲያቆሙ እና ከግጭት ቦታዎች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ በጠየቀችው መሰረት ተኩስ አቁም አድርገዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ግጭት 6 ሺ 500 ሰዎች መሞታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡