የቡድን ሰባት ሀገራት ለታዳጊ ሃገራት መሠረተ ልማት ግንባታ የሚሆን 600 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ቃል ገቡ
የቡድኑ አባል ሃገራት ጉባኤ በጀርመን በመካሄድ ላይ ይገኛል
ገንዘቡ ቻይና ከታዳጊ ሃገራቱ ጋር በ"ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ" የጀመረችውን ትብብር ለመገዳደር ያስችላል ተብሏል
የቡድን ሰባት (G7) አባል ሀገራት መሪዎች ቻይናን ለመገዳደር ያስችላል ያሉትን 600 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ቃል ገቡ፡፡
የዓለማችን ሰባት ሀብታም ሀገሮች ስብስብ የሆነው የቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤያቸውን በጀርመን እያካሄዱ ሲሆን የመወያያ አጀንዳዎች የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት፣ የኮሮና ቫይረስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቻይና ግስጋሴ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡
መሪዎቹ በትናንቱ ውሏቸው የሩሲያን ወርቅ ላለመግዛት በመወሰን ጉባኤያቸውን የከፈቱ ሲሆን በከሰዓቱ ውሏቸው ደግሞ ለታዳጊ ሀገራት መሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል 600 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ቃል ገብተዋል፡፡
ለማሰባሰብ ቃል ከተገባው ገንዘብ ወስጥ ትልቁን ድርሻ ማለትም 200 ቢሊዮን ዶላሩን የምታዋጣው አሜሪካ ስትሆን ቀሪው ደግሞ በኮታ ከቀሪ የቡድኑ አባል ሀገራት እንደሚዋጣ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጉባኤው ላይ እንዳሉት ለታዳጊ ሀገራት መሰረተ ልማት ግንባታ የተበጀተው ይህ ገንዘብ ብድር ወይም እርዳታ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ገንዘቡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚጠቅም ኢንቨስትመንት ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ታዳጊ ሀገራት ከዲሞክራሲ ጋር ተግባብተው እንዲሰሩ እድል እንደሚፈጥር በመጠቆም፡፡
አውሮፓ ደግሞ እንደ ህብረት (በአውሮፓ ህብረት በኩል) 300 ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ቃል የገባ ሲሆን በጀቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ለጤና ስራዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ ለዲጂታል ኔትወርክ ግንባታ እና ለጾታዊ መመጣጠን ስራዎች ይውላል ተብሏል፡፡
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት እንሰጠዋለን ያሉት 600 ቢሊዮን ዶላር በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ እንደሚዋጣ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በዚህ ዓመት ይሰራሉ ተብለው ከተለዩ ስራዎች መካከልም በአንጎላ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ፣ በሴኔጋል የክትባት ማምረቻ ፋብሪካ፣ እና 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ ውስጥ የቴሌ ኮሙንኬሽን መሰረተ ልማት ተጠቅሰዋል፡፡
የቴሌ ኮሙንኬሽን መስመር ዝርጋታው ከሲንጋፖር ፈረንሳይ ከዚያም በግብጽ አድርጎ ወደ ሰሜን አፍሪካ ይዘረጋል ተብሏል፡፡
ሀገራቱ በዋናነት ገንዘብ አዋጥተን ታዳጊ ሀገራትን እንደግፋለን የሚሉት ቻይና ከታዳጊ ሃገራቱ ጋር በ"ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ" የጀመረችውን ትብብር ለመገዳደር በማሰብ ነው፡፡