“የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” አመራሮች እና የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ዕርቅ ፈጸሙ
ቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንንን ጨምሮ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” በሚል በተንቀሳቀሱት አመራሮች ላይ ያስተላለፈውን እግድ አነሳ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንንን ጨምሮ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” አመራሮች ላይ ያስተላለፈውን እግድ አነሳ
“የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” አመራሮች እና የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ዕርቅ ፈጸሙ
በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” በሚል ስያሜ ሲንቀሳቀሱ የቆዩትን የእነ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንንን እግድ በማንሳት በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ውስጥ ተመድበው እንዲያገለግሉ ውሳኔ አስተላልፏል።
በቤተክርስቲያኗ እና በእነ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት ሲሰራ የቆየው የሽማግሌዎች ቡድን ተወካይ እና ቀሲስ በላይ በተፈጠረው ስምምነት ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በኦሮሚያ አካባቢ አለ ስለሚባለው የአገልግሎት መዳከም ፣ በቋንቋ የሚያስተምሩ በቂ አገልጋዮች አለመኖር እና የአስተዳደር ችግሮች ጉዳይ በሁሉም አካላት የታመነ ሲሆን ልዩነቱ መፍትሔው ላይ እንደነበር የሽማግሌ ቡድኑ ሰብሳቢ ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ ገልጸዋል፡፡ እናም የሽማግሌዎች ቡድን የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር በስተመጨረሻ ችግሮቹን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስር በሚቋቋም ጠንካራ አካል በኩል በአንድነት መፍታት የተሸለ ስለመሆኑ በሁሉም ዘንድ ታምኖበታል ብለዋል፡፡ በቅደም ተከተል ቋሚ ሲኖዶስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ባጸደቁት መሠረት የዕርቅ ሂደቱ መጠናቀቁንም ነው ላእከ ሰላም ባያብል ያረጋገጡት፡፡
የሽማግሌ ቡድኑ ሰብሳቢ ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ
እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” በሚል ሲያደርጉት የቆዩትን እንቅስቃሴ አቁመው፣ በቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ሥር ሆነው፣ ለኦሮሚያ ክልል አህጉረ ስብከት ችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት እንደሚጥሩ ከዚህ ቀደም ልዩነቱን ለመፍታት ከሚሰሩ ሽማግሌዎች ጋር መስማማታቸውን የቤተክርስቲያኗ መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህን ተከትሎ ነው የተላለፈባቸው ክህነታዊ እግድ እንዲነሳ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ የወሰነው፡፡
በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንን ጨምሮ አራት ካህናት፣ ችሎታቸው በሚመጥነው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና አገልግሎት ላይ ተመድበው ያገለግላሉ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ አፋን ኦሮሞን ጨምሮ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሥልጠና እና በመጻሕፍት ኅትመት የዕቅበተ እምነት ሥራዎች ላይ አተኩሮ የሚሠራ፣ የቋንቋዎች አገልግሎት ማስተባበሪያ ማዕከል በጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንዲቋቋም፣ በተገቢው የሰው ኃይል እና በበጀት እንዲጠናከር ውሳኔ ማሳለፉ፣ ላነሡት ጥያቄ መሠረታዊ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል እነሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን በስምምነቱ አስረድተዋል ብሏል የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ፡፡
ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን
በነሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን የሚመራው “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” እንቅስቃሴ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ከፍተኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ይስተዋላሉ የተባሉ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ሊቀ አእላፍ በላይ መኰንን የሚመሩት ኮሚቴ“የኦሮሚያ ቤተ ክህነት” ለማደራጀት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡