“ሰልፉ በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል”-አብን
አብን የጠራው ሰልፍ ውዝግብ ፈጥሯል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግድያዎችን የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በአማራ ክልል ከተሞችና በአዲስ አበባ በቅደም ተከተል ለረቡዕ ጥቅምት 18 እና ለእሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ፣ም መጥራቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ለሰልፉ ዕውቅና አለመስጠቱን አስታውቋል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የፊታችን ረቡዕ ሰላማዊ ሰልፍ መጠራቱን ገልጸው የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የአማራ ክልል እንዲረጋጋ ለማይፈልጉ ሀይሎች ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚያመች እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ የተፈጥሮ አደጋ (የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ) በተከሰተበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህጋዊ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ አል ዐይን ኒውስ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድን አነጋሯል፡፡ ኃላፊው ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና ለሌሎች የመንግስት ተቋማት ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ሕጋዊነቱን ጠብቆ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ ያስታወቁት አቶ ጣሂር መንግስት ሰላምና ጸጥታን በማስከበር ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግዛቸው ፣ የክልሉ መንግስት ምንም አይነት ሰልፍ እንዳይካሄድ መወሰኑን ገልጸው ይህን ተላልፎ ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጣ አካል ካለ የፀጥታ ኃይሉ እርምጃ እንደሚወስድ ቢገልጹም አብን ሰላማዊ ሰልፉ በታቀደለት ጊዜ መሰረት እንደሚካሄድ አረጋግጧል፡፡
ንቅናቄው በአማራ ክልል ስለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ለክልሉ መንግስት ማሳወቁን የገለጸ ሲሆን ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡