የምክክሩ ዓላማ በኢትዮጵያውያን መካከል ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሰላማዊ መፍትሔ መፈለግ ነው ተብሏል
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ሊደረግ ነው
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና የሐሳብ መንገድ በጋር ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚያመቻቹት ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንደሚደረግ ተገለጸ፡፡ የሦስቱ ተቋማት ተወካዮች ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ የተጋረጠ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ለመመከትና ሰላምን በዘላቂነት ለማምጣት ያለመ ምክክር ይደረጋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እንዳሉት በሀገሪቱ ያሉትን የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በጠረንጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ማቀራረብ እንደሚቻል ምልክቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ ዓላማዎችም በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እያወዛገቡ የነበሩ፣ ያሉና ከአሁን በኋላመ ሊከሰቱ የሚችሉ ሥር የሰደዱ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ በቅደም ተከተል ወደ ውይይት ጠረንጴዛ በማምጣት የሚፈቱበትን መንገድ መፈለግ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ችግሮቹ እንዲፈቱ የሚፈለገውም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ብቻ ይሆናል ነው የተባለው፡፡
በዚህ ሂደትም ሰፋፊ ሀገራዊና ሁሉን አቀፍ አጀንዳዎች ከልሂቃንና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰበሰቡ የተገለጸ ሲሆን በምን ርዕስ ላይ መቼ ይሁን የሚሉት ጉዳዮች የሚወሰኑት በተሳታፊዎች እንጂ በምክክሩ አመቻቾች አለመሆኑም ተገልጿል፡፡
የምክክር ሂደቱን ከማንኛውም አይነት ጣልቃ ገብነት ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑ ሥነ ስርዓቶችና መርሆች ስራ ላይ እንደሚውሉ የገለጹት የምክክሩ አመቻቾች ይህንን ሀሳብ በገንዘብም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ጫና እንዳያሳድሩ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ እርስ በእርስ የሚጋጩ የሃሳብ ልዩነቶችን ደረጃ በደረጃ ከማቀራረብ ባሻገር በተሳታፊዎች መካከል መልካም ግንኙነትን እና የአንድ ሀገር ልጅነትን መንፈስ የሚያጎለብቱ እንዲሁም መተማመንን የሚያበለጽጉ አሰራሮችን ያካትታል ተብሏል፡፡
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ንጉሱ አክሊሉ የምክክር ሂደቱ በምዕራፍ የተከፋፈለ ቀጣይነት ያለው ሂደት እንደሚሆንና ሀገራዊ ባህላዊ እሴቶችን ያማከለና ፍጹም ሙያዊ በሆነ መንገድ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
ይህ ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚካሄድ ቅድመ ግምት የተቀመጠ ሲሆን አጀንዳዎቹና ተጨማሪ ዝርዝሮች በተሳታፊዎች እንደሚወሰኑም ነው በመግለጫው ላይ የተብራራው፡፡
ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተቃራኒ አቋም የያዙ የፖለቲካ ሃይሎች እንዲገናኙ መድረኮችን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ሊገጥሟት የሚችሉ አራት ሴናሪዮዎች (እጣ ፈንታዎችን) ይፋ ያደረገ ሲሆን እነዚህም “ንጋት፣ የፉክክር ቤት፣ አፄ በጉልበቱ እና ሰባራ ወንበር” የሚሉ ናቸው፡፡