የዓለም ሀገራት መሪዎች በአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በዛሬው እለት በ73 አርፈዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶኸን፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አለ ሲሲ ኃዘናቸውን ከገጹት ውስጥ ይገኛሉ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈትን ተከትሎ የተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ ነው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትዊተር ገጻቸው ባስተላፉት መልእክት፤ ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፤ ለመላው የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ አመራሮች እና ህዝቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
የቱርኩ ፕሬዝዳነት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶኸን በተባሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት አክለውም “ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ሞት ሀዘናችንን ለመግለጽ ወደ ተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እንመጣለን” ብለዋል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም፤ በተባሩት አረብ ኢሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ፤ “ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በጣም ውድ ሰው፣ ከታላላቅ መሪዎች አንዱ እና የግብፅ እውነተኛ ወዳጅ ነበሩ” ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት፣ ዛሬ ከዚህ አለም በሞት በተለዩት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈት ማዘናቸውን በመግለጽ፤ “እስራኤል የሼክ ካሊፋን ታላቅ ስራ እና ስጦታ ታደንቃለች” ብለዋል።
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሽሃባዝ ሻሪፍም፤ “አረብ ኢሚሬትስ ታላቅ መሪ አጣች፤ እኛ ደግሞ ወድ የሆኑ ወዳጃችንን አጣን ሲሉ” ፕሬዝዳንት ሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በዛሬው ዕለት ማረፋቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
በፈረንጆቹ 1948 የተወለዱት ሼክ ኸሊፋ ከ2004 ጀምሮ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ ለቀጣዮቹ 40 ቀናት የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስናለች።
በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ስራ ዝግ እንደሚሆንም ተገልጿል።