ከአሁን ቀደምም ሊባኖስን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ቢሊዮኔሩ ነጂብ ሚካቲ በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል
ላለፉት 13 ወራት መንግስት አልባ ሆና የቆየችው ሊባኖስ አዲስ መንግስት መሰረተች፡፡
አዲስ በተመሰረተው መንግስት ነጂብ ሚካቲ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አል ሻሚ ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚካቲ የአዳዲስ ካቢኔ አባላቶቻቸውን ዝርዝር ዛሬ እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል፡፡
በቤሩት ያጋጠመው ከፍተኛ ፍንዳታ ከባድ ጉዳት ማስከተሉ እና የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ከኃላፊነት እንዲለቁ ማስገደዱ የሚታወስ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ በዚሁ ምክንያት ነበር ስልጣን የለቀቁት፡፡
ከዛ ወዲህ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዓድ ሃሪሪን ጨምሮ ተቃዋሚዎች መንግስት ለመመስረት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡
ሆኖም ዛሬ በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለትን ሂዝቦላህን ጨምሮ የአብዛኞቹን የሃገሪቱን ተቃዋሚ አካላት ድጋፍ ያገኙት ቢሊዮኔሩ ነጂብ ሚካቲ ከፕሬዝዳንት ሚሼል አውን ጋር ከተወያዩ በኋላ መንግስት ለመመስረት የሚችሉበትን ፈቃድ አግኝተዋል፡፡
በዚህም 24 አባላት ያሉት ካቢኔ (የሚኒስትሮች ምክር ቤት) አዋቅረዋል፡፡
ካቢኔው አንገብጋቢ ናቸው የተባሉ እና ክፉኛ የደቀቀውን የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለመታደግ የሚችሉ የለውጥ እርምጃዎችን የመውሰድ ትልቅ ሃገራዊ የቤት ስራ ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡
በፈረንጆቹ 2005 ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሊባኖስን ያገለገሉት ሚካቲ ከ2011 እስከ 2013ም በተመሳሳይ ሃላፊነት አገልግለዋል፡፡