ሊባኖስ የእስራኤል ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ከሀገሪቱ እንዲወጡ አሳሰበች
ሄዝቦላህ በበኩሉ ከሊባኖስ የማይወጡ የእስራኤል ወታደሮች "እንደ ወራሪ ሃይል" እንደሚቆጠሩና እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/273-155247-israel-lebonon_700x400.jpg)
በተራዘመው የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት እስራኤል ወታደሮቿን ዛሬ ሙሉ በሙሉ ከሊባኖስ ማስወጣት ይጠበቅባት ነበር
ሊባኖስ የእስራኤል ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ከሀገሪቱ እንዲወጡ አሳስባለች።
የሊባኖስ ፕሬዝዳንት እና የፓርላማው ቃል አቀባይ በጋራ ባወጡት መግለጫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የእስራኤልን ወታደሮች በፍጥነት ከሀገሪቱ እንዲያስወጣ ጠይቀዋል።
"ከሊባኖስ ያልወጡ የእስራኤል ወታደሮች እንደ ወራሪ ሃይል ይቆጠራሉ" ያለው መግለጫው ድርጊቱ ከአለማቀፍ ህግ የሚጋጭና ሉአላዊነትን የሚጥስ መሆኑንም ነው ያብራራው።
እስራኤልና ሄዝቦላህ በአሜሪካ አደራዳሪነት በህዳር ወር በደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት እስራኤል ወታደሮቿን እስከ ጥር ወር መጨረሻ ከሊባኖስ ማስወጣት ይኖርባት ነበር። ሄዝቦላህም ተዋጊዎቹን ከድንበር አርቆ የመንግስታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪዎች እንደሚሰማሩ መስማማታቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ ሳይፈጸም ቀርቶ ስምምነቱ እስከ ዛሬ (የካቲት 18 2025) መራዘሙ አይዘነጋም።
የእስራኤል ጦር ከበርካታ የሊባኖስ መንደሮች ወታደሮቹን ያስወጣ ቢሆንም ከአምስት የድንበር አካባቢዎች ግን ማስወጣት እንደማይፈልግ አስታውቋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ "ሄዝቦላህ የሚፈጽመውን የትኛውም አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመመከት ጦራችን ከአምስት የድንበር አካባቢዎች አይለቅም" ማለታቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።
የሄዝቦላህ መሪ ናይም ቃሰም በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ ከካቲት 18 በኋላ በሊባኖስ የሚታዩ የእስራኤል ወታደሮች እንደ ወራሪ የሚታዩ መሆናቸውን መናገራቸው የሚታወስ ነው። "ሁሉም ሰው ወራሪ እንዴት እንደሚስተናገድ ያውቀዋል" ሲሉም ጦርነቱ ዳግም ሊጀመር እንደሚስል አስጠንቅቀዋል።
በሊባኖስ የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ጃኒን ሄኒስ ፕላስቻርት እና በሊባኖስ የሚገኘው የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አሮልዶ ላዛሮ በጋራ ባወጡት መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አፈጻጸም ለማዘግየት የሚደረግ ጥረት "እንዲሆን የማንጠብቀው" ነው ብለዋል።
ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች በድንበር አካባቢ የሚገኙ ሊባኖሳውያን እና እስራኤላውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙም ነው ያሳሰቡት።
ሃማስ በጥቅምት 7 2023 በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት በፈጸመ ማግስት የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሮኬቶችን ተኩሷል። ለሃማስ እና ፍልስጤማውያን አጋርነቱን ለማሳየት የፈጸማቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶችም እስራኤል ጦሯን ወደ ሊባኖስ እንድታስገባና የተጠናከረ የአየር ድብደባ እንድትፈጽም አድርጓል።
በቤሩት የሄዝቦላህ መሪ የነበሩትን ሀሰን ናስራላህ የገደለችው ቴል አቪቭ ከቡድኑ ጋር ባደረገችው ውጊያ እና የአየር ጥቃት 4 ሺህ የሚጠጉ ሊባኖሳውያን ህይወታቸው አልፏል። ከ60 ሺህ በላይ እስራኤላውያን የሄዝቦላህን የሮኬት ጥቃት ሽሽት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነትን ለማስቆም በህዳር ወር 2024 የተደረሰው ስምምነት የእርስ በርስ መካሰስ ቢበዛበትም ውጥረቱን አርግቦት ቆይቷል። የእስራኤል ወታደሮቼን ሙሉ በሙሉ ከሊባኖስ አላስወጣም ማለት ግን ዳግም ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።