የቆጠቡትን ገንዘብ ማግኘት ያልቻሉ ሊባኖሳዊያን ባንኮችን በጦር መሳሪያ እያስፈራሩ ነው
ሊባኖስ በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ባንኮች ለደንበኞቻቸው ገንዘባቸውን መመለስ አልቻሉም
የሊባኖስ ባንኮች የፊታችን ሰኞ ጀምሮ በደህንነት ምክንያት ስራ ለማቆም ወስነዋል
የቆጠቡትን ገንዘብ ማግኘት ያልቻሉ ሊባኖሳዊያን ባንኮችን በጦር መሳሪያ እያስፈራሩ ነው፡፡
የመካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር ሊባኖስ በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ዜጎች በባንክ የቆጠቡትን ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም፡፡
ሊባኖስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያጋጠማት ሲሆን የሀገሪቱ መገበያያ ገንዘብም የመግዛት አቅሙ መሽመድመዱን ተከትሎ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡
አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች ፍጆታ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኢኮኖሚውን ወደ ከፋ አለመረጋጋት አስገብቶታል፡፡
በዚህም ምክንያት ባንኮች ከደንበኞቻቸው የተቆጠበ ገንዘብን መስጠት አለመቻላቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ዜጎች የጦር መሳሪያ በድብቅ እያስገቡ የባንክ ሰራተኞችን እያስፈራሩ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በየጊዜው የጦር መሳሪያ እየያዙ ወደ ባንኮች የሚያመሩ ዜጎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ባንኮች ከፍተኛ የደህንነት ችግር እንደገጠማቸው ተጠቅሷል፡፡
ለአብነትም በትናንትናው ዕለት አንዲት እንስት የካንሰር ህክምናዋን በቱርክ እየተከታተለች ለምትገኝ እህቷ ገንዘብ መላክ በመፈለግ ወደ ባንክ ብትሄድም ባንኩ ሊያስተናግዳት ባለመቻሉ የጦር መሳሪያ ለመጠቀም መገደዷን ተናግራለች፡፡
በዛሬው ዕለትም በአምስት የሊባኖስ የተለያዩ ቦታዎች የባንክ ደንበኞች የጦር መሳሪያ ተጠቅመው ገንዘባቸውን ከባንኮች ለመውሰድ መሞከራቸው ተገልጿል፡፡
የደንበኞቻቸው የጦር መሳሪያ እየያዙ መምጣት ያሳሰባቸው የሀገሪቱ ባኮችም ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት አገልግሎት ላለመስጠት መወሰናቸውን አሳውቀዋል፡፡