የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ የሊባኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየትን “ዘረኛ” ስትል አወገዘች
በተፈጠረባቸው ጫና ምክንያት ሚኒስትሩ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተገልጿል
የሊባኖሱ ሚኒስትር በኢራቅ እና ሶሪያ ለአይኤስ የሽብር ቡድን መነሳት የባህረ ሰላጤው ሀገራትን ተጠያቂ ናቸው ብለዋል
የሊባኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቻርቤል ዋህባ ሰኞ እለት አል ሁራ ከተሰኘ በአረቢኛ የሚሰራጭ የአሜሪካ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢራቅ እና ሶሪያ ለ አይኤስ የሽብር ቡድን መነሳት የባህረ ሰላጤው ሀገራትን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ እነዚህ “ወዳጅ ሀገራት አይኤስን አምጥተውብናል” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስተያየት ስድስቱን የባህረሰላጤው ሀገራት ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ሚኒስትሩ ዋህባ አስተያየቴ በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል ብለው ለማስተባበል ቢሞክሩም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ የባህረሰላጤው ሀገራት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው፡፡
የሊባኖስ ፕሬዝደንት ሚሼል አውን ፣ የሀገራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየት የግላቸው እንጂ የመንግስታቸው እንዳልሆነ እና ሊባኖስ ከባህረሰላጤው ሀገራት ጋር ያላት ወንድማማችነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ያም ሆነ ይህ ስድስቱ የባህረሰላጤው ምክር ቤት አባል ሀገራት ንግግሩን የተቃወሙ ሲሆን ከነዚህም ዩኤኢ ፣ ሳዑዲ ፣ ኩዌት እና ባህሬን በየሀገራቸው የሚገኙ የሊባኖስ አምባሳደሮችን ጠርተው አነጋግረዋል፡፡
የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር የቻርቤል ዋህባን አስተያየት “አሳፋሪ” እና “ዘረኛ” ያለ ሲሆን በሀገሪቱ የሚገኙትን የሊባኖስ አምባሳደር ጠርቶ አነጋግሯል፡፡ ዩኤኢ የሊባኖሱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስተያየት አጥብቃ እንደምትቃወም እና አስተያየታቸው ከዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ያፈነገጠ መሆኑን የሚገልጽ ኦፊሴላዊ የተቃውሞ መግለጫ ለሊባኖሱ አምባሳደር ሰጥታለች፡፡
ሳዑዲ አረቢያም ፣ የሊባኖሱ ሚኒስትር አስተያየት በሳዑዲ እና በባህረሰላጤው ሀገራት ላይ የተደረገ “ስድብ” መሆኑን ገልጻለች፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙትን የሊባኖስ አምባሳደር ጠርታ “አሳፋሪ ስድብ” ያለችውን ንግግርም ተችታለች፡፡
የሊባኖሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅም የባህረሰላጤው ሀገራት ጠይቀዋል፡፡ በሊባኖስ ፖለቲከኞችም ተቃውሞ እየደረሰባቸው የሚገኙት ሚኒስትሩ ላደረጉት ንግግር ይቅርታ ጠይቀው የስራ መልቀቂያ ደብዳቤም ማስገባታቸው ተገልጿል፡፡