በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የተወለደው አሊ 267 ዘፈኖችን አለድናቂዎቹ አድርሷል
የአንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶከተር አሊ መሃመድ ሙሳ (አሊ ቢራ) የቀብር ሥነ ስርዓት በድሬዳዋ ከተማ ተፈፀመ።
አርቲስቱ ባጋጠመው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወቃል።
ዛሬ ጠዋት የአርቲስቱ አስክሬን ቢሾፍቱ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ሽኝት የተደረገለት ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይም የጀግና የክብር ሽኝት ተደርጎለታል።
በአዲስ አበባ በተደረገው የሽኝት ስነ ስርዓት ላይም የፌደራል እና የክልል ባለስልጣናት፣ የሙያ አጋሮቹ፣ አድናቂዎቹ እና ቤተሰቦቹ ተገኝተዋል።
ከአዲስ አበባ የሽኝት መርሃ ግብር በመቀጠልም አስከሬኑ ወደ ትውልድ ከተማው ድሬደዋ ያቀና ሲሆን፤ በዚያም የሽኝት መርሃ ግብር ተደርጎለታል።
እንዲሁም በድሬዳዋ ስታዲየም የሽኝት መርሐ ግብር ከተካሄደ በኋላ የቀብር ሥነ ስርዓቱ በለገሀሬ የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።
አርቲስት ዓሊ ቢራ ከአባቱ አቶ መሐመድ ሙሣ እና ከእናቱ ወይዘሮ ፋጡማ ዓሊ በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ እንደተወለደ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።
አሊ ቢራ በ13 ዓመቱ በድምፃዊነት ሥራውን እንደ የጀመረ ሲሆን፤ 267 ዘፈኖችን አለድናቂዎቹ አድርሷል።
አሊ ቢራ ከዘፋኝነቱ ባሻገር የዜማ ደራሲ እና ሙዚቃ አቀናባሪ ሲሆን፤ ለጥለሁን ገሠሠ እና ለመሐሙድ አህመድ ጭምር ዜማዎችን ደርሷል።
ባለፉት 60 ዓመታትም ለሙያው ታምኖ የኖረው ዓሊ÷ ከድሬዳዋ እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል፡፡
አርቲስቱ ባጋጠመው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
አርቲስት ዓሊ ቢራ ከወይዘሮ ሊሊ ማርቆስ ጋር ትዳር መስርቶ ይኖር ነበር።