ኩባንያው ‘ስማርት’ ስልኮችን ማምረቱን ያቆመው በደረሰበት ኪሳራ ሲሆን ራሱን ከዘርፉ ግብይት ማግለሉንም አስታውቋል
ግዙፉ የደቡብ ኮሪያ ኤሌክትሮኒክስ አምራች ኩባንያ ኤል ጂ ራሱን ከስማርት ስልኮች ገበያ ማግለሉን አስታወቀ፡፡
ኩባንያው በገጠመው ኪሳራ ምክንያት ‘ስማርት’ ተብለው የሚጠቀሱ ዘመንኛ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ምርቶቹን ለማቆም መገደዱን አስታውቋል፡፡
ኤል ጂ በአሜሪካ የ‘ስማርት’ ስልኮች ግብይት የ10 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ ከአፕል እና ከሳምሰንግ ቀጥሎ ታዋቂ በብዙዎች የሚወደዱ ስማርት ስልኮች አምራችም ነበረ፡፡
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለኪሳራ እየተዳረገ መምጣቱ ነው የሚነገረው፡፡
ኤል ጂ በዓለም አቀፍ ገበያ የ2 በመቶ ድርሻ ነው ያለው፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ 23 ሚሊዬን ስማርት ስልኮችን በተለያዩ የዓለም ሃገራት አቅርቧል፡፡
ሆኖም ይህ በተጠቀሰው ጊዜ 256 ሚሊዬን ስልኮችን ለገበያ ካቀረበው ሌላኛው የደቡብ ኮሪያ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ ነው፡፡
ይህ ኩባንያው ምን ያህል ከዓለም አቀፍ ገበያዎች እየወጣ እንደነበር ያሳያል፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት የ4 ነጥብ 5 ቢሊዬን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰበትም ነው ሮይተርስ የዘገበው፡፡
ኩባንያው ስልክ አምራች ተቋሙን ለመሸጥ ጥረት ሲያደር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ጥረቱ አልተሳካም፡፡
ይህም በኪሳራ ከመቀጠል ይልቅ ራሱን ከገበያው እንዲያገል እና በመካከለኛ የግብይት ዋጋ ይሸጣቸው የነበሩ ሞባይል ስልኮቹን ማምረት እንዲያቆም አስገድዶታል፡፡
በስፋት በሚታወቅባቸው የቤት ውስጥ መገልገያ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ አተኩሮ ለመስራት ስለመወሰኑም ነው የተነገረው፡፡