ዩኤኢ በኢራቅ ለመልሶ ግንባታ የሚውል የ3 ቢሊዬን ዶላር ፕሮጄክት ይፋ አደረገች
“ዩኤኢ የኢራቅን እና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት ለመደገፍ ቁርጠኛ” እንደሆነች ልዑል ሞሃመድ ቢን ዛይድ ተናግረዋል
ዩኤኢ ከአሁን ቀደም በጦርነት የወደሙ የሞሱል ከተማ ጥንታዊ ቅርሶችን መልሳ ገንብታለች
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ኢራቅን መልሶ ለመገንባት የሚውል የ3 ቢሊዬን ዶላር የኢንቨስትመንት ፕሮጄክት ይፋ አደረገች፡፡
ሃገራቱ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ማድረጋቸውን ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ከሰሞኑ ሳዑዲ አረቢያ የነበሩት የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ኪዲሚ በኤሚሬት ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፉአድ ሁሴንም በጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ በተመራው ልዑክ ውስጥ ተካተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሃገራቱን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የአቡዳቢው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ተናግረዋል፡፡
በወቅታዊ ቀጣናዊ እና ሌሎችም የግንኙነት ጉዳዮች ላይ መምከራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
“ዩኤኢ የኢራቅን እና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት ለመደገፍ ቁርጠኛ ናት”ም ነው ልዑል ሞሃመድ ያሉት፡፡
ልዑሉ የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል የበላይ አዛዥ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡
ዩኤኢ በአይ ኤስ እና በጸረ አይ ኤስ ዘመቻዎች በከፊል የወደመችውን የሞሱል ከተማን መልሶ በመገንባቱ ሂደት ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር የወደሙ የከተማዋን ጥንታዊ ቅርሶች መልሶ ለመጠገንም ችላለች፡፡
ለዚህም ታዋቂው የአል ኑሪ መስጊድ እና እድሜ ጠገቡን (800 ዓመታት) የአል ጣሄራ እና የአል ሳዓ አብያተ ክርስቲያናትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሃገራቱ የጋራ የንግድ ካውንስልን ለማቋቋምም ተስማምተዋል፡፡
ኢራቅ ለሰላምና መረጋጋት ከመስራቱ ጎን ለጎን ከነዳጅ ጥገኝነት የተላቀቀ ምጣኔ ሃብትን ለመገንባት ወጥናለች፡፡
ለውጥኑ ስኬት እንደሚበጅ በማሰብም ከቀጣናው ሃገራት ጋር ተባብሮ ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋና ልዑካቸው ከሰሞኑ ተመሳሳይ ጉብኝትን በሳዑዲ አረቢያ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡