አሜሪካ በሊቢያ ምርጫ መራዘም ቅር መሰኘቷን ገለጸች
ከምርጫ በፊት በሊቢያ መዲና ትሪፖሊ እየተስተዋለ ያለው “ወታደራዊ ቅስቀሳ” የሊቢያን ተስፋ እንዳያጨልም ተሰግቷል
የሊቢያ መሪዎች “ምርጫን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሁሉንም መሰናክሎች በፍጥነት መፍታት አለባቸው”ም ተብሏል
አሜሪካ ነገ አርብ በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 እንዲካሄድ ታቅዶ በነበረው የሊቢያ ምርጫ መራዘም ቅር መሰኘቷን ገለጸች፡፡
በምርጫው ወደ የካቲት 24/ 2022 መራዘም አለመደሰታቸውን በሊቢያ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ሪቻርድ ኖርላንድ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ኖርላንድ ይህን ያሉት የሊቢያ ምርጫ ኮሚሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ለማካሄድ “አስቻይ ሁኔታዎች የሉም”በሚል ለአንድ ወር ማራዘሙን ተከትሎ ነው፡፡
ምርጫውን ወደ ቀጣዩ ወር ለማራዘም በማሰብ የቀረበው ምክረ ሃሳብም በሃገሪቱ ምክር ቤት ጸድቋል እንደ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን አፍሪካ ዘገባ፡፡
“ካለው የህዝብ ፍላጎት በመነሳት ምርጫ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ የሊቢያን ህዝብ የሚወክሉ እጩዎች ዝርዝርን ማጠናቀቅን ጨምሮ ምርጫውን ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሁሉንም የህግ እና የፖለቲካ መሰናክሎች በፍጥነት መፈታት አለባቸው”ም ብለዋል አምባሳደሩ፡፡
አሜሪካ የሀገራቸውን የወደፊት እድል ለመወሰን በሚያስችለው ምርጫ ለመሳተፍ የተዘጋጁ ሊቢያውያንን ስጋት እንደምትጋራም ገልጸዋል፤ በትሪፖሊ እና በሌሎች ከተሞች ያለውን የጸጥታ ስጋት እንዲረጋጋም የጠየቁት አምባሳደሩ፡፡
በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድጋፍ ተልዕኮ ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በስተደቡብ እየተደረገ ያለው ወታደራዊ ቅስቀሳ እንደሚያሳስበው ትናትናው መግለጹ የሚታወስ ነው።
ሁኔታው ሃገሪቱን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ በመሆኑ ሁሉም ኃይሎች ከመሰል ተግባር እንዲታቀቡ አሳስቧል።
የተመድ መግለጫን ይዘት የሚጋሩት በሊቢያ የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛና አምባሳደር ሪቻርድ ኖርላንድም ሁሉም የሊቢያ ኃይሎች ለሊብያ ሰላምና መረጋጋት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ የመጨረሻውን የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረግ አለማቻሉን ተከትሎ፤ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ ደቡባዊ ትሪፖሊ የታጠቁ ቡድኖች ወታደራዊ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መታየታቸው በሊቢያ የተሰነቀውን ተስፋ እንዳያጨልም ተሰግቷል።