ፖለቲካ
የሊቢያ ፓርላማ ለዲቤባ መንግሥት ይሁንታ ሰጠ
በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ያሳለፈችው ሊቢያ የአንድነት መንግስት ለመመስረት ተቸግራ ዓመታትን ማሳለፏ የሚታወቅ ነው
ዲቤባ 35 አባላት ያሉት ካቢኔ እንዲያዋቅሩም ፓርላማው ፈቅዷል
የሊቢያ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በአብዱል ሃሚድ ዲቤባ ለሚመራው ‘የብሄራዊ አንድነት’ መንግስት አብላጫ የመተማመኛ የድጋፍ ድምጽ ሰጠ፡፡
የዲቤባ መንግስት 50+1 የድጋፍ ድምጽ በሚጠይቀው የምርጫ ሂደት ከ132ቱ የምክር ቤቱ አባላት የ121ዱን የድጋፍ ድምጽ አግኝቷል፡፡
ድጋፉ በሰፊ ልዩነቶች የሚታወቀው ፓርላማ ወደ አንድ መምጣቱን የሚያሳሳይ ነው ተብሏል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አጉይላ ሳሌህም ቀኑን “ታሪካዊ” ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸውታል፡፡
ምክር ቤቱ የዲቤባ መንግስት 35 አባላት ያሉት ካቢኔ እንዲያዋቅርም ፈቅዷል፡፡
የአዲሱ የሊቢያ መንግስት መሪው አብዱል ሃሚድ ዲቤባ መመረጣቸውን ተከትሎ ታድያ በቀጣይ ለምርጫ ኮሚሽኑን አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ሀገራቸው ሊቢያ በመጪው ታህሳስ 2021 የምታከናውነውን ምርጫ እውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የ‘የብሄራዊ አንድነት’ መሪው አብዱል ሃሚድ ዲቤባ ፓርላማው ለሰጣቸው ይሁንታ ያመሰገኑ ሲሆን፤ በቀጣይ በሊቢያ ምድር የአብሮነትና አንድነት መንፈስ እንዲያብብ ለማድረግ እና ያለፈውን የመከፋፈል ጊዜ ለማካከስ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡