ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ “የስልጣን ጊዜ በአራት ዓመታት ብቻ የሚገድብ” ምክረ-ሃሳብም አቅርቧል
በሊቢያ የሚገኘው ከፍተኛ የመንግስት ምክር ቤት መጪውን የፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ ወደ የካቲት 2022 ለማራዘም የሚያስችል ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
ምክረ-ሃሳቡ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን በየካቲት 2022 ከፓርላማ ምርጫ ጋር በአንድ ጊዜ ለማካሄድ የሚል ሲሆን ፤ በአንድ ጊዜ ማካሄዱ ፕሬዚዳንታዊ እንዲሁም ሁለት ምክትል እና የጠቅላይ ሚኒስትር ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የሚቋቋመው ፓርላማ ዋና ተግባር ለሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት እንደሚሆንም ምክር ቤቱ ገልጿል።
ምክር ቤቱ የመጪውን የፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ የስልጣን ጊዜ በአራት ዓመታት ብቻ እንዲገደብም ሀሳብ አቅርቧል።
ጅምሩ ስኬታማ እንዲሆን ብሔራዊ መግባባት መጀመር፣ በፓርቲዎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ እና መንግሥት ለምርጫው ተገቢውን ምህዳር መስጠት ትለቅ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁሟል።
የካውንስሉ ሊቀመንበር ካሊድ አል መሽሪ መራጮች በመጪው ምርጫ እንዳይሳተፉ ማሳሰባቸውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡትን የምርጫ ህጎች "አሳፋሪ" በማለት ባለፈው ወርሃ ህዳር መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡
በታኅሣሥ 24 ለማካሄድ ታቅዶ በቆየው ምርጫ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ የሊቢያ መራጮች ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የቀድሞ የሊቢያ መሪ የሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ በሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ግምት ተስጥቷቸዋል።
ከወደ ምስራቅ ሊብያ የተገኙት ጠንካራው ካሊፋ ሃፍታር፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሀሚድ ዲቤባህ እና የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋ በሊብያ ምርጫ የሚጠበቁ እጩዎች ናቸው።
ሁለቱም ፕሬዚዳንታዊ እና የህግ አውጭ ምርጫዎች ለታህሳስ 24 ተይዘው የነበረ ቢሆንም፤ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ፓርላማው የድምጾቹን ቀናት በመከፋፈል የህግ አውጪ ምርጫዎችን ፤ የአሁኑ ምክረ-ሃሳብ ሳይቀርብ በፊት እስከ ወርሃ ጥር ድረስ እንዲራዘም ማድረጉ ይታወሳል።