የሊቢያን ችግር ለመፍታት የውጭ ኃይሎች መውጣት አለባቸው ተባለ
የሊቢያ ጎረቤቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ዛሬ በአልጄሪያ ተሰብስበዋል
በሊቢያ ጉዳይ በሚመክረው ስብሰባ ላይ የተመድ መልዕክተኛ ተገኝተዋል
በሊቢያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፤ የውጭ ኃይሎች ከሀገሪቱ መውጣት እንዳለባቸው አልጄሪያ አስታወቀች፡፡
የሊቢያ ጎረቤቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሀገሪቱ ሁኔታ ላይ ዛሬ በአልጄርስ ተሰብስበዋል።
የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ የትሪፖሊ የሰላም መንገድ ሊመጣ የሚችለው የውጭ ኃይሎች ከሀገሪቱ ለቀው ሲወጡ እንደሆነ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የውጭ ሀገራት ሊቢያን የጉልበት ማሳያ እና የሃይል ሚዛን ማስጠበቂያ ማድረግ ሊቆም እንደሚገባም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
በሊቢያ ያለው ቀውስ ሊፈታ የሚችለው በሊቢያውያን ጥረት እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ መሆኑን የገለጹት የአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የሊቢያ ጎረቤቶችም በሀገሪቱ ያለው ችግር በቀጥታ እንደሚመለከታቸው ተናግረዋል።
የዛሬው ስብሰባ ጎረቤት ሀገሮች በሀገሪቱ ሰላም እንዲመጣ መጫወት ያለባቸውን ሚና ለማሳየት ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ሊቢያን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የጎረቤቶቿ ሚና ወሳኝ በመሆኑ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በሊቢያ ታህሳስ 24 ቀን ምርጫ እንዲደረግ ቀነ ቀጠሮ መያዙን ያነሱት ሚኒስትሩ ለዚህም ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል። ይህ ሀገሪቱን ወደ መረጋጋት የማምጣት ሂደት እና የሊቢያን ተቋማት የማዋሃድ ስራ እንደሚቀጥልም ነው የተገለጸው።
ይህም በሀገሪቱ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲኖር እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፤ በተቻለ ፍጥነት ግን የውጭ ኃይሎች መውጣት እንዳለባቸው የአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
አሁን ላይ ሊቢያ የገጠማት ችግር እና የደረሰችበት ደረጃ ከጎኗ መቆምን እና ውጤታማ ድጋፍን የሚጠይቅ እንደሆነም በስብሰባው ተገልጿል።
ዛሬ ሊቢያን በተመለከተ በሚመክረው የአልጄሪያው ስብሰባ ላይ በሊቢያ ተባበሩትመንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ጃን ኩቢስ፤ የአረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ እና የጎረቤት ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።