ፓርላማው ፋቲ ባሻጋን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙን አስታውቋል
የሊቢያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙን አስታወቀ፡፡
ምክር ቤቱ ፋቲ ባሻጋን በአብደል ሃሚድ አል ዲቤይባ ምትክ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በአብላጫ ድምጽ መሾሙን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ካድ አል ቢባስ የተባሉ እጩ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸውን ተከትሎ ባሻጋ ያለምንም ተቀናቃኝ ብቸኛ እጩ ሆነው መቅረባቸውንና በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ባሻጋ በዲቤይባ አስተዳደር ስር በሃገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴርነት በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ ሆኖም ዛሬ ዲቤይባን ተክተው የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃገሪቱን ወደ ተረጋጋ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ሊመልስ የሚችል መንግስት ያዋቅራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ ያደረጉ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አግባቢነት ከአንድ ዓመት በፊት ጊዜያዊ መንግስትን መስርተው ሲመሩ የነበሩት ዲቤይባ በበኩላቸው የፓርላማውን ውስኔ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
እሳቸውን ያለ ምርጫ ከስልጣን ለማስወገድ የተደረገ እንደሆነም ነው በመናገር ላይ ያሉት፡፡ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው እስከሚታወቅ ድረስ መንግስታቸው በስልጣኑ እንደሚቆይም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ሃገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች መራዘሙ ይታወሳል፡፡ ዲቤይባ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ተረፉ መባሉ አይዘነጋም፡፡