ለሊቢያ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ወደ ፖለቲካ ሂደት መመለስ እንደሚያስፈልግ ተ.መ.ድ. ገለጸ
ሊቢያ ከአውሮፓውያኑ 2011 ወዲህ ሰላም እንደራቃት ትገኛለች
በሀገሪቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
ለሊቢያ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ወደ ፖለቲካ ሂደት መመለስ እንደሚያስፈልግ ተ.መ.ድ. ገለጸ
በሊቢያየተባበሩት መንግስታት የድጋፍ ተልዕኮ (UNSMIL) በእርስ በእርስ ጦርነት ዉስጥ በምትገኘው ሊቢያ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ወደ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት መመለስ አስፈላጊ መሆኑን አሳሰበ፡፡
ተልዕኮው ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የሊቢያን ህዝብ ወካይ መንግስት የመመስረት ፣ የክብር እና የሰላም ፍላጎት ለማሳካት ሙሉ እና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት መጀመር አስፈላጊ መሆኑን የሚያረጋግጡ ክስተቶች በሊቢያ እየታዩ ነው ብሏል፡፡
በሀገሪቱ መረጋጋትእንዲሰፍን ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና ሁሉም ዜጎች ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ የሚችሉበት እድል እንዲፈጠር አጥብቆ አሳስቧል፡፡
ተልእኮው በመላው ሊቢያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ ዜጎችን ያለአግባብ በቁጥጥር ስር የማዋል እና በእንቅስቃሴ እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ እንዲሁም የመሰብሰብ መብት ጥሰቶች በስፋት እየተፈጸሙ ስለመሆኑ ሪፖርቶች እንደሚደርሱት ገልጿል፡፡
በተለይም በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወሰደው ከመጠን በላይ የኃይል እርምጃ እንዲሁም በርካታ ዜጎችን ያለ አግባብ በቁጥጥር ስር የማዋል ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተልዕኮው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2011 ከሙአማር ጋዳፊ ዉድቀት እና ሞት በኋላ ሊቢያ ሁከትና የፖለቲካ አለመረጋጋት መገለጫዋ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሀገሪቱ ሁለት ዋነኛ ተቀናቃኞች ከጥቂት ቀናት በፊት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸውን ቢገልጹም አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን አላከበረም በሚል በመወነጃጀል ላይ ናቸው፡፡
ዘገባው የሲጂቲኤን ነው፡፡