ከቀድሞው የሊቢያ መሪ ሞአማር ጋዳፊ ውድቀት በኋላ ሀገሪቱ እርስበእስር ግጭት ውስጥ ገብታለች
የሊቢያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ግብፅ መዲና ካይሮ መብረር መጀመሩን አስታወቀ፡፡
አየር መንገዱ ከሰባት ዓመታት በኋላ 255 ሰዎችን አሳፍሮ ከሙዓይቲቃ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ወደ ካይሮ መድረሱም ተገልጿል፡፡
የሊቢያ አየር መንገድ ወደ ግብፅ በረራ አድርጎ የነበረው ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ማለትም በፈረንጆቹ 2014 ነበር፡፡ በሀገሪቱ ባለው ቀውስ ምክንያትም በረራው ተስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የግብፅ ባለስልጣናት ከሊቢያ አውሮፕላን ማረፊያዎች ወደ ካይሮ የሚደረጉ በረራዎችን አግደው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሊቢያን ለረጅም አመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሙአማር ጋዳፊ በህዝባዊ አመጽ ከተወገዱ በኋላ በሀገሪቱ በተፈጠሩ ሁለት ቡድኖች እስካሁን ድረስ ጦርነት እየተካሄደ ነው፤የውጭ ሀይሎች በሁለቱም ጎራ በመግባት ግጭቱን ሲያባብሱት ቆይተዋል፡፡