ተመድ በሊቢያ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በ“ውጭ ተዋጊዎች እየተጣሰ ነው” ሲል አስታወቀ
የጥቅምት ወር ስምምነቱ የውጭ ተዋጊዎች 90 ቀናት ባለሞላ ጊዜ ሊቢያን ለቀው ይውጡ የሚል ነበር
ተዋጊዎቹ የሶርያ፣ ሩስያ፣ሱዳን እና ቻድ ናቸውም ብለዋል የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ
በሊቢያ ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት ተኩስ ለማቆም ስምምነት ላይ ቢደረስም “የውጭ ተዋጊዎች” ስምምነቱን እየጣሱ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ፡፡
ጉቴሬዝ ትናንት ተሰብስቦ ለነበረው የድርጅቱ የፀጥታው ም/ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት በሊቢያ የተቋቋመው አዲስ የሽግግር መንግስት ወደ ኃላፊነት መምጣቱ “ለሀገሪቱና ተቋማቶቿ አንድነት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ተስፋ” የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከተደረሰው ስምምነት ውጭ 20 ሺህ ገደማ “የውጭ ተዋጊዎች” አሁንም በሊቢያ ይገኛሉ፡፡
ተዋጊዎቹ የሶርያ፣ ሩስያ፣ሱዳን እና ቻድ እንደሆኑም በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ተግዳሮቶች ቢኖሩም ሊቢያ በመጪው ወርሃ ታህሳስ ለምታካሂደው ምርጫ መሳካት በፓለቲካው፣ኢኮኖሚውና የፀጥታው መስኮች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አጠናክራ ልትቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡
በሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር /ኔቶ/ የታገዘው የ2011ዱ ህዝባዊ አመፅ ሙዓማር ጋዳፊን መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡
ይህንን ተከትሎም በመዲናዋ ትሪፖሊ ውስጥ በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት በሚታገዙ ኃይሎች እና በሀገሪቱ ምስራቅ ውስጥ ባሉት ተቀናቃኝ ባለሥልጣናት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሊቢያ ለዓመታት በሁከት ስትናጥና ሳትረጋጋ ቆይታለች፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው ተፋላሚ ወገኖች በታጠቁ ቡድኖች እና በውጭ መንግስታት ጭምር የሚደገፉ መሆናቸው ነው እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡
እናም አሁን የተሰነቀው ተስፋ ከዳር ለማድረስ ሀገሪቱ በመመራት ላይ ያለው የ“ብሄራዊ አንድነት መንግስት” በፀጥታ መዋቅሩ ላይ ለሚያካሂደው ሪፎርም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል አንቶንዮ ጉቴሬዝ፡፡
ጥቅምት 2020 የተደረሰው ስምምነት በሊቢያ የሚገኙ የውጭ ታጣቂዎችና ተላላኪዎች 90 ባልሞሉ ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚል እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡