ተመድ ከምርጫ በፊት በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ የሚደረግ “ወታደራዊ ቅስቀሳ ያሳስበኛል” አለ
ወታደራዊ ቅስቀሳው በሊብያ የተሰነቀውን ተስፋ እንዳያጨልም ተሰግቷል
የምርጫ ኮሚሽን “የመጨረሻውን የእጩዎች ዝርዝር ይፋ አለማድረጉ” ለወታደራዊ ቅስቀሳዎቹ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል
በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድጋፍ ተልዕኮ ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በስተደቡብ እየተደረገ ያለውን ወታደራዊ ቅስቀሳ እንደሚያሳስበው ገለጸ።
ተልእኮው ባወጣው መግለጫ፤ በትሪፖሊ እየተስተዋሉ ያሉ አሉታዊ ለውጦች መረጋጋትን እና የጸጥታ ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ በመሆናቸው ሁሉም ኃይሎች ከመሰል ተግባር እንዲጠነቀቁ አሳስቧል።
ሁሉም የሊቢያ የፖለቲካ ተዋናዮች "በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የሊቢያን እድገት የሚጠብቅ፣ ሰላማዊ ምርጫ እና የተሳካ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችል፤ የደህንነት እና የፖለቲካ ሁኔታ ለመፍጠር በጋራ እንዲሰሩ" ተልእኮው በመግለጫው ጠይቋል።
ይህንን ግብ ለማሳካት በሊቢያ የተመድ ዋና ፀሃፊ ልዩ አማካሪ ስቴፋኒ ዊሊያምስ በአሁኑ ጊዜ የሊቢያ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰሩ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
የምርጫ ኮሚሽኑ የመጨረሻውን የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረግ አለማቻሉን ተከትሎ፤ ከትናንት ማክሰኞ ጠዋት ጀምሮ ደቡባዊ ትሪፖሊ የታጠቁ ቡድኖች ወታደራዊ ቅስቀሳ ሲያደረጉ መታየታቸው በሊብያ የተሰነቀውን ተስፋ እንዳይጨልም ተሰግቷል።
ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል በሚል ስጋት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ከባድ መሳሪያዎች በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የአከባቢው ነዋሪዎች መግለጻቸውም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የሊቢያ ምርጫ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ አማካኝነት በሊቢያ የፖለቲካ ውይይት መድረክ በየካቲት ወር የፀደቀው ፍኖተ ካርታ አካል ሲሆን፤ ዓላማውም በሊቢያ መረጋጋትን ለማምጣት መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።
በሊቢያ በሚካሄደው ምርጫ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ መራጮች ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቀድሞ የሊቢያ መሪ የሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ በሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ግምት ተስጥቷቸዋል።
ከወደ ምስራቅ ሊብያ የተገኙት ጠንካራው ካሊፋ ሃፍታር፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሀሚድ ዲቤባህ እና የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋ በሊብያ ምርጫ የሚጠበቁ እጩዎች ናቸው።