የሊቢያን ምርጫ በሚያስተጓጉሉ ጉዳዮች ላይ “አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ” ተመድ አሳሰበ
በምርጫው ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ መራጮች ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል
ያሳለፍነው አርብ ይካሄድ የነበረው ምርጫ ለአንድ ወር መራዘሙ ይታወሳል
በሊቢያ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ዋና አማካሪ የሊቢያ ህግ አውጭዎች ምርጫን ሊያስተጓጉሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ 'አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጡ' አሳሰቡ፡፡
ዋና አማካሪው ስቴፋኒ ዊሊያምስ በሀገሪቱ የሚጠበቀውን የፓርላማ እና ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲሳካ ህግ አውጭዎች “ማንኛውም እንቅፋት ሊሆን የሚችልን ነገር ሊፈቱ ይገባል”ም ብለዋል፡፡
ስቴፋኒ ዊሊያምስ ይህን ያሉት፤ የሊቢያ የተወካዮች ምክር ቤት በታህሳስ 24 ቀን ምርጫውን ለማካሄድ የማይቻልባቸውን አዳዲስ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ስብሰባ መቀመጡን ተከትሎ ነው፡፡
“የሕዝብ ተወካዮች የምርጫውን ሂደት ወደ ፊት ለማራመድ ከፍተኛ ብሔራዊ ምርጫ ኮሚሽን ለሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች በአስቸኳይ ምላሽ በመስጠት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ነው ዋና አማካሪዋ ያስታወቁት፡፡
ከአስር አመታት በላይ በግጭት ስትታመስ በነበረችው ሊቢያ የሚካሄደው ምርጫ በሀገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ የሚከፍት ነው ተብሎ ቢጠበቅም፤ ድፍን አንድ አመት የሞላው ሂደት በከፍተኛ ፈተናዎች መታጀቡ ጉዳዩ የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ተስፋ እንዳያጨለም ተሰግቷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ እና ጣሊያን በሊቢያ ምርጫ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሊቢያ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድጋፍ ተልዕኮ በበኩሉ፤ የምርጫ ኮሚሽኑ የመጨረሻውን የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረግ አለማቻሉን ተከትሎ ከዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በስተደቡብ እየተደረገ ያለው ወታደራዊ ቅስቀሳ እንደሚያሳስበው ገልጾ ነበር።
ተልእኮው ባወጣው መግለጫ፤ በትሪፖሊ እየተስተዋሉ ያሉ አሉታዊ ለውጦች መረጋጋትን እና የጸጥታ ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ በመሆናቸው ሁሉም ኃይሎች ከመሰል ተግባር እንዲጠነቀቁም አሳስቧል።
በሊቢያ በሚካሄደው ምርጫ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ መራጮች ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቀድሞ የሊቢያ መሪ የሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳኢፍ አል ኢስላም ጋዳፊ በሊቢያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ከወዲሁ ግምት ተስጥቷቸዋል።
ከወደ ምስራቅ ሊቢያ የተገኙት ጡረተኛው የጦር ጄነራል ካሊፋ ሃፍታር፣ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሀሚድ ዲቤባህ እና የቀድሞ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፋቲ ባሻጋም በሊቢያ ምርጫ የሚጠበቁ ሌሎች እጩዎች ናቸው።