በሊቢያ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ የገቡ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
በሀገሪቱ ደርና በተባለችው ከተማ በደረሰው የጎርፍ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ሺህ እንደሚደርስ ተገምቷል
በምዕራብ እና ምስራቅ ያሉ የሊቢያ መንግስታት አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል
በሊቢያ ምስራቃዊ ክፍል የደረሰው አሰቃቂ የጎርፍ አደጋ በጥቂቱ የ5 ሺህ 300 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
ደርና የተባለችው ከተማ ከንቲባ የሟቾቹ ቁጥር ከ18 እስከ 20 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ገልጸዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቀለው አደጋ አለማቀፉ ማህበረሰብ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ለማቅረብ አስገድዷል።
ሊቢያን የሚመሩት ሁለት መንግስታትም በዚህ አስከፊ ጊዜ በትብብር እየሰሩ ነው ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት።
በምስራቅ እና ምዕራብ የራሳቸውን መንግስት ያቋቋሙት ተፋላሚ ሃይሎች አለማቀፍ ጥሪ ማቅረባቸውንና የሰብአዊ ድጋፎችን በማድረስ ረገድም እየተባበሩ ስለመሆኑ የአለም ፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሃላፊ ታውሂድ ፓሻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሊቢያ የረጅም ጊዜ መሪዋ ሙአመር ጋዳፊ በ2011 ከተገደሉባት በኋላ የጸና መንግስት ማቋቋም ተስኗት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።
ጦርነቱ ተቀማጭነታቸውን በትሪፖሊ እና ቱብሩክ ያደረጉ መንግስታት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ ድቤባ በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈውን የብሄራዊ አንድነት መንግስት ትሪፖሊ ላይ ሆነው ይመራሉ።
በምስራቅ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሳማ ሃማድ የትሪፖሊውን አስተዳደር የሚፋለም መንግስት ይመራሉ፤ ይሁን እንጂ የምስራቁ መንግስት በጀነራል ካሊፋ ሃፍጣር የበላይነት የሚዘወር መሆኑ ይነገራል።
ባለፈው እሁድ ከተከሰተው አደጋ በኋላ እነዚህ ሁለት የሊቢያ መንግስታት በትብብር እየሰሩ ነው መባሉ መልካም ዜና ቢሆንም ከአለማቀፉ ማህበረሰብ እየቀረበ ያለው ድጋፍ ግን አነስተኛ ነው ብሏል አይኦኤም።
ተንታኞች ግን አለማቀፍ እውቅና ያለው መንግስት የምዕራቡ (ትሪፖሊ የሚገኘው) በመሆኑና አደጋው የደረሰው በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በመሆኑ የሰብአዊ ድጋፉ ሊጓተት እንደሚችል ያነሳሉ።
በሊቢያ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ለጀነራል ካሊፋ ሃፍጣር ድጋፍ እንደምሰጥ የሚነገርላት ግብጽ ወደ ሊቢያ ሰብአዊ ድጋፍ ልካለች። ድጋፉን ትሪፖሊ ድረስ በማቅናት ያስረከቡትም የግብጽ ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ኦሳማ አስካር ናቸው።
በጎርፍ አደጋው ህይወታቸው ያለፈ 80 ግብጻውያን አስከሬንም ወደ ሀገራቸው እንዲመለስ ተደርጓል።
በመንግስታቱ ድርጅት የሚደገፈውን መንግስት (የምዕራቡን) ለማገዝ በ2020 ወታደሮቿን ለማስገባት እስከመወሰን የደረሰችው ቱርክም 160 የነፍስ አድን ሰራተኞቿን ልካለች።
ቱኒዚያ፣ ጣሊያን እና ስፔንም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቻቸውን ወደ ሊቢያ ደርና ከተማ ልከዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሀገራት በጦርነት ለደቀቀችውና አስከፊ የጎርፍ አደጋ ለደረሰባት ሊቢያ ፈጥነው እንዲደርሱ አሳስቧል።