በትግራይ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በዋሉ የራያ እና አላማጣ አካባቢዎች ህይወት ምን ይመስላል?
የራያ እና አላማጣ አካባቢ ነዋሪዎች በፌደራል መንግስት “ተከድተናል የሚል ስሜት ውስጥ መግባታቸውን” ተናግረዋል
የትግራይ ታጣቂዎች ከአላማጣ 15 ኪሎ ሜት ራዲያስ ውስጥ ሆነው በየቀኑ ተጨማሪ ሀይል እያስገቡ ነው ተብሏል
በትግራይ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በዋሉ የራያ እና አላማጣ አካባቢዎች ህይወት ምን ይመስላል?፡፡
የቀድሞው የትግራይ ልዩ ሀይል በክልሉ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው እና ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡
ይህ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ጦርነቱ ቢቆምም ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ የትግራይ ታጣቂዎች ወደ ራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መግባታቸውን ተከትሎ የዳግም ጦርነት ስጋት ደቅኗል፡፡
የአማራ ክልል በህወሃት ታጣቂዎች ወረራ ተፈጽሞብኛል ቢልም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር ግን ጉዳዩ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ አንድ አካል ነው ብሏል፡፡
ይህን ተከትሎ አል ዐይን አማርኛ በትግራይ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር በዋሉ የራያ እና አላማጣ አካባቢዎች ህይወት ምን ይመስላል ሲል ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡
ስማቸው ለደህንነታቸው ሲሉ እንዳይጠቀሱ የፈለጉ በአላማጣ አቅራቢያ ባለችው አዶሬ ቀበሌ የሚኖሩ አንድ አርሶ አደር እንዳሉን መፍትሔ ልናገኝ ነው ብለን ስንጠብቅ ለዳግም ስቃይ ተጋልጠናል ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው እንዳሉት “የትግራይ ታጣቂዎች ከመጡበት ዕለት አንስቶ ንብረታችን እየተነጠቀ ነው፡፡ ለገበያ የደረሰ ሀብ ሀብ አትክልቴን በልተውብኛል ሲጠግቡ ደግሞ በያዙት ጦር መሳሪያ በሰደፉ እና በአፈሙዙ እየመቱብኝ ነው” ብለዋል፡፡
በቀበሌያችን ከገቡበት ከሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በገበሬው ቤት እየገቡ እየመቱን ነው ያሉት እኝህ አርሶ አደር ጦር መሳሪያ አምጡ እያሉ እኛ ገበሬዎች ነን ፖለቲካ አናውቅም ብንልም ሊተውን አልቻሉም ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ ከዚህ በፊት አብረውን ይኖሩ የነበሩ ነገር ግን በስጋት ምክንያት ወደ ትግራይ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ካሳለፍነው ሰኔ እና ግንቦት ወር ጀምሮ እየገቡ መኖር ጀምረዋል፣ ሳይገቡ የቀሩት ከዚህ በፊት በነበረው አስተዳድር ጊዜ ህዝብን ሲያንገላቱ እና ሲያማርሩ የነበሩት ብቻ ቀርተው ነበርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በአላማጣ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የትግራይ ታጣቂዎች አላማጣን በ15 ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ከበው እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ታጣቂዎች ሲቪል እየለበሱ ወደ ከተማዋ ነዋሪ መስለው እየገቡ ነው፣ የመንግስት ተቋማትን እየዘረፉ እና ፋይሎችን እያወደሙ የከተማዋ ነዋሪዎችንም ፍርሃት ውስጥ እንዲገባ የተለያዩ ጫናዎችን እያደረጉ ነው የሚሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ በከተማዋ ያለው የፌደራል የጸጥታ ሀይል ቢኖርም ነዋሪውን ከመሰደድ እንዳልታደገውም ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ለራያ እና አላማጣ ጉዳይ ዘለቄታዊ መፍትሔ ይሰጠዋል ብለን እየጠበቅን ለትግራይ ታጣቂዎች አሳልፎ ሰጥቶናል ያሉት አስተያየት ሰጪው ህዝቡ ተከድተናል የሚል ስሜት ውስጥ መግባቱንም አክለዋል፡፡
በሰሌን ውሃ ቀበሌ የሚኖረው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ የትግራይ ታጣቂዎች የራያ እና አላማጣ የገጠር ቀበሌዎችን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቆጣጠራቸውን፣ በየቀኑ አዳዲስ እና ተጨማሪ ታጣቂዎች ወደ አካባቢዎቹ እየገቡ መሆኑን አክሏል፡፡
ታጣቂዎቹ በየሰው ቤት እየገቡ የልጆችን ምግብ ሳይቀር እየበሉ እንደሆነ፣ ለባሏ የምሳ እቃ ለማድረስ ወደ እርሻ ቦታ እየሄደች ያለችን እናት ለአማራ ታጣቂ ልትሰጪ ነው በሚል እያንገላቱ ነው ያሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ ታጣቂዎቹ ይህን ሲያደርጉም የፌደራል የጸጥታ ሀይሎች እያዩ የማስቆም ፍላጎት እንደሌላቸውም ነግሮናል፡፡
ከዚህ በፊት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ወደ መቀሌ እና ሽሬ የሄዱ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ ቤታቸው ተመልሰው አብረን በጋራ እያረስን እና እየኖርን ቢሆንም ታጣቂዎቹ በድንገት መጥተው ለእንግልት እንደዳረጓቸውም አክሏል፡፡
ታጣቂዎቹ በየጊዜው እየሰበሰቡም ከእንግዲህ እምናስተዳድራችሁ እኛ ነን፣ የያዛችሁትም የአማራ ክልል የነዋሪነት መታወቂያ ከእንግዲህ አይጠቅማችሁም፣ ልጆቻችሁን አምጡ እና ለአማራ ታጣቂዎች ድጋፍ እያደረጋችሁ ነው የሚሉ ወከባዎችን እያደረሱባቸው እንደሆነም እኝህ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል፡፡
ወቅቱ የሚያዚያ ወር አዝመራ የምናዘምርበት ቢሆንም እርሻችንን ትተን በየቀኑ ምን እንሆን ይሆን የሚል ስቃይ ውስጥ ነን የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሁሌ በስደት እና በእንግልት መኖር ሰልችቶናል ዘለቄታዊ መፍትሔ ይሰጠን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ከአላማጣና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 50 ሺህ ማለፉን ተመድ አስታወቀ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር መንግስት ወደ ራያ እና አላማጣ የገጠር ቀበሌዎች የገቡ ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው እንግልት ዙሪያ ያለውን ምላሽ ለማካተት የደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
የፌደራል መንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በአካባቢው ነዋሪዎች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን በእጅ ስልካቸው ላይ ብንደውልም በጽሁፍ እንድንልክላቸው ከነገሩን በኋላ እና ጉዳዩን ከነገርናቸው በኋላ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሰባት ምዕራባዊን ሀገራት በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች እንደ አዲስ የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የተመድ ሰብዓዊ መብት ድርጅት በበኩሉ በራያ እና አላማጣ አካባቢዎች በተከሰተው አዲስ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉን መናገሩም አይዘነጋም፡፡