በአወዛጋቢዎቹ የራያ አካባቢዎች ግጭት መከሰቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት መግለጫ አወጣ
የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮ እንደገጸው በእነዚህ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎች 50ሺ ደርሷል
ሊቀመንበሩ ሁለቱም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲታቀቡ እና የአካባቢውን ንጹሃን መፈናቀል እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርዋል
የአማራ እና የትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አላማጣ እና አካባቢዋ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት በአወዛጋቢዎቹ ራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፎላ "በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ያሉ ውጥረቶችን" በትኩረት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጿል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተደረሰው የፌደራል መንግስት እና የህወሓት የዘላቂ ሰላም ስምምነት፣ ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸው "አወዛጋቢ ቦታዎች" በህገመንግስቱ መሰረት እልባት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ይጠቅሳል።
ሊቀመንበሩ ሁለቱም ወገኖች ግጭት ከማባባስ እንዲታቀቡ እና የአካባቢውን ንጹሃን መፈናቀል እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርዋል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የጠየቁት ሊቀመንበሩ ለአወዛጋቢ ቦታዎች መፍትሄ ይሰጣል ያሉት የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ጠይቀዋል።
የፌዴራል መንግስት የራያ አካቢዎችን ጨምሮ በሌሎች አወዛጋቢ አካባቢዎች የፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይል እንደሚሰማራ እና አካባቢዎች በህዝበ ውሳኔ ወደፈለጉበት እንዲካለሉ እንደሚደረግ ገልጾ ነበር።
ይሁን እንጂ መንግስታዊ መዋቅር ዘርግቶ የራያ አላማጣ እና አካባቢዎቹን እያስተዳዳረ የነበረው የአማራ ክልል መንግስት፣ ህወሓት የፕሪቶረመያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሶ ለአራተኛ ዙር ወረራ እንደከፈተበት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ከሶ ነበር።
የክልሉ መንግስት በዚህ መግለጫው፣ ህወሓት ወደ ግጭት እንዳይገባ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል ጥረት ቢያደርግም፣ ካለፉት ጦርነት አልተማረም ያለው ህወሓት ጦርነት እንደከፈተበት ገልጿል።
ህወሓት ወሯቸዋል ካላቸው የራያ አካባቢዎችም እንዲወጣም በመግጫው ጠይቋል።
የተመድ የሰብአዊ መብት ቢሮ እንደገጸው በእነዚህ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎች 50ሺ ደርሷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስዳደር ግን ደቡብ ትግራይ በሚለው ዞን ውስጥ ባሉ አወዛጋቢ ቦታዎች እየሆኑ ያሉ አዳዲስ ሁነቶች በስምምነቱ መሰረት የተደረጉ ናቸው ይላል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው የአማራ ክልል ካወጣው መግለጫ ቀደም ሲል በትዊተር ገጻቸው በራያ እና በሌሎቹ አወዛጋቢ አካባቢዎች ያሉት ሁነቶች በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው፤ ከአማራ ክልልም ይሁን ከፌደራል መንግስት ጋር ግጭት ማለታቸው ይታወሳል።
ህወሓት ስምምነት ጥሶ ወረራ ፈጽሞብኛል ስለሚለው የአማራ ክልል መንግስት መግለጫም ይሁን ሁነቶች በስምምነቱ መሰረት እየተካሄዱ ናቸው ስለሚለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስተያየት የፌደራል መንግስት ያለው የለም።
ስምምነትቱን ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ የፌደራል መንግስት እና ህወሓት አንዳቸው ሌላኛቸውን ሲወቅሱ እንደነበር ይታወሳል።