በኡጋንዳ በ2020 እና 2011 የደረሱ የመብረቅ አደጋዎች 30 የሚጠጉ ሰዎችን ህይወት ቀምተዋል
በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር መብረቅ የ14 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ተነገረ።
በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ላምዎ ወረዳ የደረሰው አደጋ 34 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንም የኡጋንዳ ፖሊስ አስታውቋል።
አደጋው ፓላቤክ በተሰኘው የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ መድረሱን የፖሊስ ቃልአቀባይ ኪቱማ ሩሶኬ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
ኡጋንዳ ከደቡብ ሱዳን በምትዋስንበት ድንበር ላይ የሚገኘው የስደተኞች ጣቢያ ከ80 ሺህ በላይ (አብዛኞቹ ደቡብ ሱዳናውያን) ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አመላክቷል።
“ሰዎች ለጸሎት በተሰባሰቡበት ምሽት 11 ስአት አካባቢ ዝናብ መዝነብ ጀመረ፤ ከ30 ደቂቃ በኋላም ሃይለኛ ነጎድጓድና መብረቅ ተሰማ” ነው ያሉት የፖሊስ ቃልአቀባዩ።
በኡጋንዳ ምስራቃዊ ክፍል አሩዋ በተሰኘችው ከተማ ከአራት አመት በፊት በደረሰ የመብረቅ አደጋ 10 ህጻናት ህይወታቸው አልፏል።
ህጻናቱ እግርኳስ ሲጫወቱ ቆይተው እረፍት በማድረግ ላይ እያሉ በመብረቅ ተመትው መሞታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
በፈረንጆቹ 2011ም ከመዲናዋ ካምፕላ በ210 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው ኪርያንዶንጎ ከተማ ትምህርት ቤት ላይ የወደቀ መብረቅ 18 ተማሪዎችና መምህራንን ህይወት መቅጠፉ ይታወሳል።
ኡጋንዳ በአለማችን በመብረቅ በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ከሚያልፍባቸው ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትገኛለች።
መዲናዋ ካምፓላም በአመት ውስጥ በርካታ ቀን በመብረቅ ከሚመቱ የአለማችን ከተሞች አንዷ መሆኗን የአለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት መረጃ ያመላክታል።