ኢትዮጵያ በሊማው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4ኛ የወርቅ ሜዳልያዋን አገኘች
ሻምፒዮናው ዛሬ ምሽት ሲጠናቀቅም ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳልያዎችን እንደምታገኝባቸው የሚጠበቁ ውድድሮች ይካሄዳሉ
ኢትዮጵያ በአለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሜዳልያ ብዛት አሜሪካን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች
በፔሩ ሊማ እየተካሄደ በሚገኘው የአለም ከ20 አመት በታች የአትሌቲክ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን አገኘች።
ትናንት ሌሊት በተደረጉት የሴቶች 3 ሺህ ሜትር እና የወንዶች 800 ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል።
አትሌት አለሽኝ ባወቀ በ8 ደቂቃ ከ50.32 ሰከንድ በመግባት በ3 ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ስታስገኝ፥ አትሌት ማርታ አለማየሁ ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ነሃስ አስገኝታለች።
አትሌት ጀነራል ብርሀኑ ደግሞ በ800 ሜትር ውድድር በአንደኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን፥ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 1 ደቂቃ ከ46:86 ሰከንድ ፈጅቶበታል።
ሻምፒዮናው ዛሬ ምሽት የሚጠናቀቅ ሲሆን ኢትዮጵያ እስካሁን አራት የወርቅ፣ ሁለት የብር እና አንድ የነሀስ በድምሩ ሰባት ሜዳልያዎችን ማግኘት ችላለች።
ከኢትዮጵያ ጋር እኩል አራት የወርቅ ሜዳልያ ያላት አሜሪካ በብር እና ነሃስ ሜዳልያዎች በመብለጥ የሊማውን ከ20 አመት በታች አትሊቲክስ ሻምፒዮና የደረጃ ሰንጠረዥ እየመራች ነው።
በሻምፒዮናው አትሌት ሲምቦ አለማየሁ 3000 ሜትር መሰናክል የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ማሸነፏ ይታወሳል።
አትሌት መዲና ኢሳም በ5 ሺህ ሜትር ውድድር ለሀገሯ የወርቅ ሜዳልያ ማስገኘቷ አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ ምሽት ሜዳልያዎችን የምትጠብቅባቸው ውድድሮች ይካሄዳሉ።
የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች፣ የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና የወንዶች 1500 ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች ላይ የሚመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያ ሻምፒዮናውን በቀዳሚነት እንድታጠናቅቅ ሊያደርጋት እንደሚችል ተገምቷል።