ኔቶ የዩክሬን ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ዘልቃ መግባት ህጋዊ ነው አለ
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ኬቭ እርምጃውን ስትወስድ ኔቶን አላሳወቀችም፤ ድርጅቱ በሩሲያው ዘመቻ ምንም ድርሻ የለውም ብለዋል
የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ድንበር ጥሶ ከገባ 26ኛ ቀኑን ይዟል
ዩክሬን ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ክልል ድንበር ጥሳ መግባቷ ህጋዊ ነው አሉ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ከጀርመኑ ቬት አምሶንታግ ጋዜጣ ባደረጉት ቆይታ “ዩክሬን ራሷን መከላከል ትችላለች፤ በአለማቀፉ ህግ መሰረት ራስን የመከላከል መብት በራስ ድንበር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም” ብለዋል።
ኬቭ ወደ ሩሲያ ዘልቃ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም ማቀዷን አስቀድማ ለኔቶ አለማሳወቋንም ነው ዋና ጸሃፊው ያነሱት።
በዚህም 32 አባላት ያሉት ወታደራዊ ጥምረት 26ኛ ቀኑን ከያዘው “ዘመቻ” እና “ወረራ” ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ተናግረዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ዩክሬን የጀመረችው ጥቃት አደጋ እንዳለው በማንሳትም ወታደራዊ ዘመቻውን እንዴት እንደምትፈጽመው ለኬቭ መተው ይሻላል ሲሉም ተደምጠዋል።
የንስ ስቶልተንበርግ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጦራቸው ወደ ሩሲያ የገባው በቀጣይ ጥቃት እንዳይፈጸም ለመከላከል የሚሆን ቀጠና ለማግኘት በማሰብ ነው ማለታቸውን በማውሳትም የኬቭን የመከላከል መብት ህጋዊነት ለማሳየት ሞክረዋል።
ከኬቭ ጋር ጦርነት ያማዘዛት የኔቶ መስፋፋት መሆኑን የምታነሳው ሩሲያ ግን ጥቃቱን “ከባድ ጸባ አጫሪነት ነው” ማለቷ ይታወሳል።
ሞስኮ ወደ ግዛቷ የገባውን የዩክሬን ጦር በአጭር ጊዜ እንደምታስወጣ ብትዝትም በፈረንጆቹ ነሃሴ 6 የገባው ጦር እስካሁን ከሩሲያ ግዛት ሙሉ በሙሉ አልወጣም።
የሩሲያ ጦር የዩክሬን ጦር ላይ ከባድ ጥቃት ከማድረስ ይልቅ በምስራቃዊ ዩክሬን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸውን ከተሞች እየተቆጣጠረ ይገኛል።
ኔቶም ሆነ እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት ከዩክሬን ዘመቻ ጋር በተያያዘ የምናውቀው የለም ቢሉም ክሬምሊን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን መግለጹ አይዘነጋም።
የሩሲያን ወደ ዩክሬን መዝለቅ “ወረራ” ነው ሲሉ የቆዩት ምዕራባውያን እና አለማቀፍ ተቋማት የአሁኑን የኬቭ ወደ ሩሲያ መግባት “ህጋዊ መብት” አድርገው እያቀረቡት ነው።