ባርሴሎና ሜሲን ለ2 ዓመታት ሊያስፈርመው ይችላል የሚሉ መላምቶችም እየተሰሙ ነው
የስፔኑ ባርሴሎና የእግር ኳስ ኮከቡ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር የነበረው ኮንትራት መጠናቀቁ ይፋ የሆነ።
የስድስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የበርካታ ክብሮች ባለቤቱ አርጀንቲናዊው ኮከብ ከካታሎኑ ክለብ ጋር የነበረውን ውል ማብቃቱን ተከትሎ፤ ቀጣይ ማረፍያው የት ይሆናል የሚለው በርካቶች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የ34 ዓመቱ የእግር ኳስ ምትሀተኛ ከወዲሁ በበርካታ ክለቦች ዓይን ውስጥ መግባቱንም ነው የጎል ዶት ኮም መረጃ የሚያመላክተው።
ነገር ግን ባርሴሎና ሊኔል ሜሲን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በካምፕ ኑ እንዲቆይ ሊያደርገው ይችላል የሚሉ አስታየቶች ቢኖሩም፤ ማንችስተር ሲቲ እና ፒ.ኤስ.ጂ ሜሲን ከሚፈልጉ ታላላቅ ክለቦች ውስጥ ናቸው ተብሏል።
በከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ የሚገኘው ባርሴሎና ሜሲን እንደገና ለማስፈረም ሊቸገር እንደሚችልም እየተገለጸ ይገኛል።
የተጫዋቹ የባርሴሎና ውል ማለቁን ተከትሎ መገናኛ ብዙሃን በርካታ ግምቶች እያስቀመጡ ቢሆንም፤ ሀገሩን ወክሎ በኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይ በሚገኘው ሜሲ እስካሁን ስለ ጉዳዩ ያለው ነገር የለም።
አሁን ላይ የሊዮኔል ሜሲ ትኩረት መጪው ቅዳሜ ሀገሩ አርጀንቲና እና ኢኳዶር የሩብ ፍጻሜ የምታካሂደው ጨዋታ መሆኑም ነው የተገለጸው።
አርጀንቲናዊው ኮከብ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2000 አንሰቶ ለባርሴሎና ሲጫወት መቆየቱ የሚታወቅ ነው።
በክለቡ ቆይታው የስድስት የባላንዶር እንዲሁም ስድስት የአውሮፓ ወርቅ ጫማ አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ ክለቡ ባረሴሎና ባደረገቸው የላሊጋ፣ ከፓ.ዲ.ላሬ እና የቻምፕዮንስ ሊግ ጫወታዎች 34 ዋንጫዎችን ያነሳ ታላቅ የእግር ኳስ ኮከብ ነው።