“በፓሪስ በእግር ኳስ ህይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በጉጉት እየጠበኩ ነው”- ሊዮኔል ሜሲ
ከባርሴሎና ጋር የተለያየው ሊዮኔል ሜሲ በሁለት ዓመት ኮንትራትን ፓሪስ ሴንት ዠርሚያ (ፒኤስጂ) ተቀላቀለ።
በትናትናው እለት በሁለት ዓመት ኮንትራት ፓሪስ ሴንት ዠርሚያ (ፒ.ኤስ.ጂ) የተቀላቀለው ሜሲ ኮንትራቱ ለ3ኛ ዓመት ሊራዘም እንደሚችልም አማራጭ ቀርቦለታል ነው የተባለው።
የ34 ዓመቱ ሜሲ በእግር ኳስ ዘመኑ እስካሁን በክለብ ደረጃ ለባርሴሎና ብቻ ተጫወተ ሲሆን፤ በመጨረሻም ከክፍያ ጋር በተያያዘ ክለቡን ለመልቀቅ ተገዷል።
ባርሴሎና በአዲሱ የላሊጋ የፋይናንሻል ህግ መሰረት ለሊዮኔል ሜሲ አዲስ ኮንትራት ማቅረብ ባለመቻሉ ነው ተጫዋቹን ለመልቀቅ የተገደደው።
ይህንን ተከትሎም የ34 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በሁለት ዓመት ኮንትራትን የፈረንሳዩን ፓሪስ ሰን ዠርሚያ (ፒኤስጂ) መቀላቀሉ እውን ሆኗል።
በትናትናው እለት ከክለቡ ጋር በይፋ የተፈራረመው ሜሲ፤ “በፓሪስ በእግር ኳስ ህይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር በጉጉት እየጠበኩ ነው” ብሏል።
“በክለቡ ውስጥ ልዩ ችሎታ እና ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች እንዳሉ አውቃለሁ” ያለው ሜሲ፤ “ለክለቡ እና ለደጋፊዎች የተሸለ ትልቅ ነገር ማድረግ ይጠበቅብኛል” ሲልም ተናግሯል።
የክለቡ ፕሬዚዳንት ናስር አል ከላይፊ በበኩላቸው፤ “ሊዮኔል ሜሲ ፓሪስ ሴንት ዠርሚያን በመምረጡ በጣም ደስተኞች ነን " ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ።
ሊዮኔል ሜሲ በነጻ ዝውውር ፒኤስጂን ተቀላቀለ አራተኛው ተጫዋች ሲሆን፤ በክለቡም 30 ቁጥር ማሊያን እንደሚለብስ ተነግሯል።
ፓሪስ ሴንት ዠርሚያ ክልብ ውስጥም የዓለማችን ውድ ከተባሉ ሁለት ተጫዋቾች ማለትም ከኔይማር እና ከኪሊያን ምባፔ ጋር ጥምረት እንደሚፈጥርም ታውቋል።
አርጀንቲናዊው ኮከብ የእግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር የስፔኑ ባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብን የተቀላቀለው።
ሜሲ በባርሴሎና ቆታውም በ778 ጨዋታዎች ላይ ተሳተፎ 672 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ ሲሆን፤ ይህም ከበረ ወስን ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ሊዮኔል ሜሲ በባርሴሎና ቆይታው 6 ጊዜ የባላንድኦር ተሸላሚ መሆን የቻለ ሲሆን፤ ከካታላኑ ክለብ ጋር በመሆንም 35 ዋንጫዎችን በማንሳት ችሏል።