እንግሊዝ ዴንማርክን 2ለ1 በሆነ ውጤት በመርታት ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ መድረስ ችላለች
ለአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ የደረሰችው እንግሊዝ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር መከሰሷ ተነግሯል።
ክሱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከዴንማርክ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ በዴንማርኩ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል ፊት ላይ አረንጓዴ ቀለም ያለው ብርሃን በመደረጉ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም የእንግሊዝ ደጋፊዎች የዴንማርክ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ረብሻ ሲፈጥሩ እንደነበር ተገልጿል። ድርጊቱ የተፈጸመው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም ቅጣት ምት ባገኘበት ወቅት መሆኑም ተነግሯል።
የክሱ ሂደት በእግር ኳስ ማህበሩ የቁጥጥር ስነምግባር እና ዲሲፕሊን ክፍል እንደሚታይ ተገልጿል።
የብሪታኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ደጋፊዎቹ የደንማርክ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር መጮህ እንዳልነበረባቸው ተናግረው ደጋፊዎች ይህንን ከማድረግ ይልቅ መከባበርን መምረጥ አለባቸው ብለዋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጉዳዩን እያው መሆኑን አንስተው እነሱ ግን እንደዚህ አይነት ረብሻ ማየት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ሜዳው ላይ ከዋናዋ የመጫወቻ ኳስ ባለፈም ሌላ ኳስ ወደ ሜዳ ገብቶ እያለ ዋናው ዳኛም ሆኑ ረዳት ዳኞቹ ጨዋታውን ማስቆም ሳይችሉ መቅረታቸው ለትዝብት እንደዳረጋቸው ሜል ስፖርት ዘግቧል።
ራሂም ስተርሊንግ በቀኝ ክንፍ በኩል ኳስ ይዞ ሳለ ከዋና የመጫወቻ ኳስ ውጭ ሌላ ኳስ መግባቱ ጨዋታውን ሊያስቆመው ይገባ እንደነበርና ጨዋታው ባለመቆሙም ተጫዋቹ ኳሱን ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ይዟት ሲገባ ከዴንማርኩ ተከላካይ ጋር በመነካካቱ ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጥቷል።
የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን ቀድሞ ግብ ማስቆጠር ቢችልም እንግሊዝ ግን ጨዋታውን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ዕሁድ ጣሊያንን ትገጥማለች።
ራሂም ስተርሊንግ ከአይ ቲቪ ጋር ባደረገው ቆይታ ፍጡም ቅጣት ምቱ መሰጠቱ ተገቢ ነወይ ተብሎ ሲጠየቅ በትክክልም ፍጹም ቅጣት ምት ያሰጥ እንደነበር ተናግሯል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሳውዝጌት በበኩላቸው ፍጹም ቅጣት ምቱን ያሰጣል አያሰጥም ለማለት በደንብ እንዳላዩት ተናግረዋል።
የዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል አባትና የቀድሞው ግብ ጠባቂ ፔተር ሽማይክል ለቢን ስፖርት በሰጠው አስተያየት የጨዋታው ዳኛ የሰጡት ፍጹም ቅጣት ምት ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።
የአርሰናል የቀድሞ አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር በማታው ጨዋታ የተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት አግባብ አለመሆኑን አንስተው፤ ዳኛው በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነትን ለምን እንዳላከበሩ ጠይቀዋል።