በእስራኤል ጥቃት ስጋት ምክንያት የቤሩት ነዋሪዎች ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ ገብተዋል
እስራኤል እና ሄዝቦላ፣ የሀማስ እና እስራኤል ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በድንበር አካባቢ ተኩስ እየተለዋወጡ ይገኛሉ
የሄዝቦላ የጦር አዛዥ ሹኩር በቤሩት እና የሀማስ የፖለቲካ መሪ ሀኒየህ ቴህራን መገደላቸው በቀጣናው የነበረው ውጥረት እንዲጦዝ አድርጎታል
በእስራኤል ጥቃት ስጋት ምክንያት የቤሩት ነዋሪዎች ከፍተኛ መረበሽ ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።
የእስራኤል ተዋጊ ጄቶች፣ በኢራን የሚደገፈው የሄዝቦላ መሪ ንግግር ከማድረጉ ትንሽ ቀደም ብለው ከ30 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በቤሩት አየር ላይ ከፍተኛ ድምጽ ማሰማታቸው በከተማው ያሉ ነዋራዎች መደበቂያ ለማግኘት እንዲሯሯጡ አድርጓለዋል።
የጦር አውርፕላኖቹ በቤሩት ከተማ ሰማይ ላይ ዝቅ ብለው መብረራቸውን ሮይተርስ የአይን አማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።አውሮፕላኖቹ ሲያሰሙት የነበረው ድምጽ በአመታት ውስጥ በቤሩት የተሰማ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የሄዝቦላ ከፍተኛ የጦር አዛዥ ፉአድ ሹኩር በቤሩት ደቡባዊ ዳርቻ እና የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መገደላቸው በቀጣናው የነበረው ውጥረት እንዲጦዝ አድርጎታል።
እስራኤል ለሹክር ግድያ ኃላፊት ስትወስድ፣ ስለሀኒየህ ግድያ ግን ምን አይነት አስተያያት አልሰጠችም። ኢራን እና ሀማስ ግን እስራኤል ግድያውን መፈጸሟን እና ለዚህም የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ መዛታቸው ይታወሳል።
ሄዝቦላ፣ ሀኒየህ ከተገደለ ከሰአታት በኋላ ለተፈጸመው የጦር አዛዡ ግድያ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል።
የሄዝቦላ መሪ የሆኑት ሰኢድ ሀሰን ነስረላህ ውጤት ምንም ቢሆን እስራኤል ባለፈው ሳምንት በጦር አዛዡ ላይ ለፈጸመችው ግድያ "ጠንካራ እና ውጤታማ" ምላሽ እንደሚሰጥ በትናንትናው ተናግሯል። መሪው አክሎም ሄዝቦላ ትክክለኛውን ሰአት እየጠበቀ መሆኑን እና ሰአቱ መቼ እንደሚሆን ፍንጭ መስጠት አንደማይፈልግ ገልጿል።
ሄዝቦላ የበቀል እርምጃ እንዳይወስድ የተደረጉ አለምአቀፍ ጥረቶች አልተሳኩም ብሏል ነስረላህ።
"ምንም አይነት ውጤት ቢያስከትል፣ እነዚህ የእስራኤል ጥቃቶች ያለ ምላሽ አይታለፉም"ሲል ነስረላህ በቤሩት የተገለውን የሄዝቦላ አዛዥ አንደኛ ሳምንት ለማሰብ ለተሰበሰበ ህዝብ ተናግረዋል።
እስራኤል እና ሄዝቦላ፣ የሀማስ እና እስራኤል ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በድንበር አካባቢ ተኩስ እየተለዋወጡ ይገኛሉ። በቅርቡ ያለው ውጥረት ሁለቱን አካላት ወደ አጠቃላይ ጦርነት እንዳያስገባቸው ተሰግቷል።