የገና በዓልን ማክበር ክልክል የሆነባቸው 15 የዓለማችን ሀገራት
የገና በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድን አስመልክቶ የሚከበር በዓል ነው
የተወሰኑ የዓለማችን ሀገራት የገና በዓል እንዳይከበር የከለከሉ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ አማኝ ባለመኖሩ ምክንያት እንደ ማንኛውም ቀን በስራ ያልፋል
የገና በዓልን ማክበር ክልክል የሆነባቸው የዓለማችን ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ተከትሎ የገና በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ይህ በዓል በተለያዩ ሀገራት እንደ እምነቱ፣ ባህልና ወግ መሰረት በታህሳስ ወር ከሁለተኛው ሳምንት ጀምሮ በተለያየ መንገድ የሚከበር ዓለም አቀፍ በዓልም ነው።
በአሜሪካ እና በአውሮፓ የገና በዓል ከአዲስ ዓመት በዓላቸው ጋር አቀናጅተው ስራ ትተው እና ቢሮ ዘግተው በደማቁ ያከብሩታል።
ብዙዎቹ ሀገራት በገና በዓል ዕለት መደበኛ ስራዎችን በመዝጋት በቤታቸው ተሰብስበው ያከብሩታል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን የገና በዓል ምን እንደሆነ የማያውቁ እና በዓሉን ከነጭራሹ የማያከብሩ ሀገራት እንዳሉ ያውቁ ይሆን?
የፊታችን አርብ በሚከበረው የገና በዓል የፍስክ ምግብ ይበላል?
ቻይና የገና በዓልን ከማያከብሩ የዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ስትሆን ዕለቱም እንደሌሎች የስራ ቀን ተብሎ ያልፋል።
ቻይና በይፋ ሀይማኖት የሌላት ሀገር ስትሆን የገናን በዓል ማክበርም ህገወጥነት ነው ተብሏል።
አፍጋኒስታን ሌላኛዋ የገናን በዓል የማታከብር ሀገር ስትሆን አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች ሙስሊሞች መሆናቸው ለበዓሉ አለመከበር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀሪያ ሌላኛዋ የገና በዓል የማይከበርባት ሀገር ስትሆን በተለይም ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ከፈረንጆቹ 1962 ጀምሮ የገናን በዓል አክብራ አታውቅም።
98 በመቶ የእስልምና እምነት ተከታዮች ህዝብ ያላት ኮሞሮስ የገናን በዓል የማታከብር ሌላኛዋ የዓለማችን ሀገር ናት።
ሊቢያ እና ሞሪታንያ የገና በዓል የማይከበርባቸው ተጨማሪ የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች አለመኖር ደግሞ ለበዓሉ አለመከበር ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል።
እስያዊቷ ሞንጎሊያ የገና በዓል የማይከበርባት ስትሆን የሀገሪቱ ዜጎች የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ናቸው ተብሏል።
ሌላኛዋ የኢየሱስ ክርስቶች ልደት ወይም ገና የማይከበርባት ሀገር አመጸኛዋ ሰሜን ኮሪያ ናት። በዚህ ሀገር የገናን በዓል ማክበር ለእስር እና ተጨማሪ ቅጣት መደንገግ የሚያስችል ህግ ማውጣቷ ተገልጿል።
ፓኪስታን ሌላኛዋ ገናን የማታከብር የዓለማችን ሀገር ስትሆን ዓለም በታህሳስ 25 በየዓመቱ የገናን በዓል ሲያከብር እሷ ግን የፓኪስታን መስራች የሚባሉትን መሀመድ አሊ ጅናህን አስባ ትውላለች።
በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ሳውዲ አረቢያ የገናን በዓል ማክበር የከለከለች ሀገር ስትሆን በዓሉን የሚያመለክት የገና ዛፍ እና ሌሎች መሰል ድርጊቶችን ማከናወን እና በንግድ ቦታዎችም ይዞ መገኘት እንዲሁም መሸጥ ለቅጣት ይዳርጋል ተብሏል።
ከሰሞኑ ከወደብ ስምምነት ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ መግባቷን የገለጸችው ጎረቤት ሀገር ሶማሊያም የገና በዓል ከማይከበርባቸው ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ተብላለች፡፡
ይህች የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ የገና በዓል በሀገሯ እንዳይከበር በይፋ በህግ ያገደች አፍሪካዊት ሀገር እንደሆነች ተገልጿል።
ከሶማሊያ በተጨማሪም ታጃኪስታን፣ ቱኒዝያ፣ኡዝበኪስታን እና የመን የገና በዓል በሀገራቸው እንዳይከበር ህግ የደነገጉ እና ሲያከብሩ የተገኙ ዜጎችን ከሚቀጡ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።