የፊታችን አርብ በሚከበረው የገና በዓል የፍስክ ምግብ ይበላል?
የዘንድሮው የገና በዓል ከሁለት ቀናት በኋላ የፊታችን አርብ ይከበራል
“ገና አርብ ላይ ሲውል በዋዜማው ሀሙስ የ‘ጋድ ጾም’ ይጾማል”-መጋቢ አእላፍ ፋሲል ታደሰ
የዘንድሮው ገና በዓል የፊታችን አርብ ዕለት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተናግራለች፡፡
ገና ወይም የልደት በዓል የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ታሳቢ አድርጎ የሚከበር ነው፡፡
ያለፉትን ከ40 የላቁ ቀናት በጾም እና በጸሎት ያሳለፉት ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶች በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች፣ በመብላት በመጠጣት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ያከብሩታል፡፡
ገና በመጣ ወቅት የፍስክ ምግቦችን መብላት መጠጣቱ መገባበዙ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም የዘንድሮው በዓል የፊታችን አርብ የሚከበር መሆኑን ተከትሎ ብዙዎቹ የቤተ እምነቱ ተከታዮች በዕለቱ የፍስክ ይበላ ይሆን በሚል እየጠየቁ ነው፡፡
አንዳንዶች በዕለቱ አንዳንዶች ደግሞ በማግስቱ ቅዳሜ እንደሆነም የፍስክ ምግብ የሚበላው እየተነጋገሩ ይገኛሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛም ይህንኑ ጉዳይ በመያዝ የበዓሉን አከባበር በማስመልከት ከሰሞኑ ቡራኬ ልትሰጥ እንደምትችል የምትጠበቀውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ጠይቋል፡፡
በአዲስ አበባ የቀበና ምስራቅ ጸሃይ መድኃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል የሆኑት መጋቢ አእላፍ ፋሲል ታደሰ የገና ጾም ወይም ጾመ ነቢያት 44 ቀናት እንዳሉት ፣ከዚህ ውስጥ 40ዎቹ ቀናት የነቢያት ጾም ሲባሉ ሶስቱ ቀናት የሶሪያዊው አብርሃም እንዲሁም አንዱ ቀን ደግሞ ጋድ ጾም መሆናቸውን ታምናለች ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ታህሳስ 29 የሚከበረው የገና የዘንድሮው በዓል አርብ ዕለት ላይ እንደሚውል ስብከተ ወንጌሉ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በዓሉ አርብ ላይ ሲውል ሀሙስ ደግሞ ‘ጋድ ጾም’ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች በተለይም ጾመ ነቢያትን ሲጾሙ የቆዩ ሰዎች ወይም ጾሙን ከአርብ እና እሮብ ውጪ መጾም ያልቻሉ ነግር ግን ነፍሰ ጡሮች እና ህሙማን አርብ መፈሰክ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡
የበዓሉ ቅዳሴ እና ቁርባን ሌሊት ላይ ስለሚካሄዱ አርብ እለት ቀን ጀምሮ የዕምነቱ ተከታዮች መፈሰክ እንደሚችሉ መጋቢ አእላፍ ፋሲል ተናግረዋል፡፡
አርብ እና እሮብን ሳይጾሙ የቆዩ ሰዎች ግን ጋድ ጾምን ብቻ በመጾም የልደት በዓልን ማክበር እንደማይችሉም ስብከተ ወንጌሉ ገልጸዋል፡፡
ጾመ ነቢያት ወይም የገና ጾም ነቢያት በየዘመናቸው የዓለም ነቢያት ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ ይወለዳል በሚል አምነው ሲጾሙ እና ሲጸልዩ ያሳለፉትን መከራ ለማሰብ የሚጾም መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ታምናለች፡፡