ለአባቶች ቀን በዓል ሰውነታቸው የተገላለጠ ዳንሰኞችን የጋበዘው ከንቲባ አነጋጋሪ ሆኗል
ከንቲባው ዳንሰኞቹን ያመጣሁት ዕለቱን አይረሴ እና ለየት ለማድረግ በማሰብ ነው ብሏል
ጉዳዩ ቀስ እያለ መታወቁን ተከትሎ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው
ማኑኤል ኤንጅል የተባለው ሰው በሜክሲኮዋ ቺያፓስ ግዛት ስር ያለችው ሁዌሁታን የተሰኘች ከተማ ከንቲባ ነው።
ይህ ከንቲባ ከአንድ ወር በፊት የተከበረውን የዓለም አባቶች ቀንን ለማክበር በሚል ጥሪ ያቀርባል።
የበዓሉ ጥሪ ለአባቶች ብቻ ነው የተባለ ሲሆን ህጻናት እና ሴቶችን ይዞ መምጣትም ክልክል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
ይህ የአባቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እያለ ሰውነታቸው የተገላለጠ ዳንሰኞች ወደ አዳራሹ ትዕይንት ማቅረቢያ ይመጣሉ።
ከንቲባው ያስተባበረው ይህ በዓል አባቶች በዓሉን ለየት ባለ መንገድ እንዲያከብሩት በማሰብ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
ለበዓሉ የተጋበዙ አባቶችም በዓሉን በደስታ ማሳለፋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አጋርተዋል።
ይሁንና ቆየት እያለ የበዓሉ ትክክለኛ አከባበርን የሚገልጹ ምስሎች እየተለቀቁ መምጣታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
በዓሉን ያስተባበረው ከንቲባም ትችቶችን ያስተናገደ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ከንቲባውን እያደነቁ ጽፈዋል።
የከተማዋ ከንቲባም ለእርቃን የተቃረቡት ዳንሰኞችን የጋበዘው አባቶች በዓሉን ለየት ባለ እና አይረሴ በሆነ መልኩ እንዲያከብሩ በማሰብ መሆኑን ተናግሯል።
ይሁንና ከንቲባው የሰራው ስራ ትክክል እንዳልሆነ የሚገልጹ ትችቶች አሁንም በመቅረብ ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን ከንቲባው እስካሁን ይቅርታ አለመጠየቁም ተዘግቧል።