ማንቺስተር ሲቲ ነጥቡ ሊቀነስ እና ወደ 2ኛው ዲቪዥን ሊወርድ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡
ማንቺስተር ሲቲ ነጥቡ ሊቀነስ እና ወደ 2ኛው ዲቪዥን ሊወርድ እንደሚችል ተጠቆመ፡፡
ያለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ማንቺስተር ሲቲ፣ የክለቦች ፍትኃዊ የገንዘብ አወጣጥ ህግን (Financial Fair Play rules) ጥሷል በሚል፣ ከትናንት በስቲያ ለሁለት ዓመታት ከሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር መታገዱ ይታወቃል፡፡
ከዚህም ባለፈ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 25 ሚሊዮን ፓውንድ ቅጣትም በክለቡ ላይ ጥሏል፡፡
ሲቲ ህጉ ከሚፈቅደው በላይ ለተጫዋች ግዢ ወጪ ለማውጣት በመፈለግ፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 እና 2016 የስፖንሰርሺፕ ገቢውን አጋኖ አቅርቧል ተብሎ ነው ቅጣቱ የተጣለበት፡፡
ዴይሊ ስታር እንደዘገበው የፕሪሚየር ሊጉ ኮሚቴ ደግሞ ክለቡን በነጥብ ቅነሳ ሊቀጣው ይችላል፡፡ ከዚህም ባለፈ በቅርቡ በወጣው አዲስ ህግ መሰረት ሲቲ ወደ ሁለተኛው ዲቪዥን ወርዶ እንዲጫወትም ሊደረግ ይችላል ተብሏል፡፡
ይህ ማለት ደግሞ ከዓለማችን ገናና ክለቦች አንዱ የሆነው ሲቲ ወደ ታች ወርዶ እጣ ፋንታውን ከነ ግሪምስቢ ታውን፣ ፎረስት ግሪን እና መሰል ክለቦች ጋር በማድረግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ ፍሊሚያ ለማድረግ ይገደዳል፡፡
ክለቡ በቀጣዩ ዓመት የደርቢ ውድድሩን የሚያደርገው ከከተማ ተቀናቃኙ ማንቺስተር ዩናይትድ ጋር ሳይሆን በአቅራቢያው ከሚገኘው የቀድሞ የዩናይትድ ዝነኛ ከዋክብት ፊል እና ጋሪ ኔቭል፣ ኒኪ ቡት፣ ፓውል ስኮልስ፣ ርያን ጊግስ እና ዴቪድ ቤካም ክለብ ከሆነው ሳልፎርድ ሲቲ ጋር ሊሆንም ይችላል፡፡
የሳልፎርድ ሲቲ ባለቤቶች-ፎቶ ጌቲ ኢሜጅ
ሊጉ እርምጃወውን የሚወስደው፣ ክለቦች ለአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እንደሚያቀርቡት ሁሉ ለፕሪሚየር ሊጉም ስለ ክለባቸው ትክክለኛ መረጃ እንዲያቀርቡ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ነው፡፡
ቅጣቱ በፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ሆነው ለማጠናቀቅ ለሚወዳደሩ ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታን ለማግኘት እድል የሚፈጥርላቸው ነው፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ኮሚቴ አባላት፣ ሲቲ ከሻምፒዮንስ ሊግ መታገዱ ከጸና በክቡ ላይ ስለሚጣልበት የነጥብ ቅነሳ ውይይት ማድረጋቸውም በዘገባው ተጠቁሟል፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን ውሳኔ ለማስቀልበስ ጥረት እንደሚያደርጉ የሲቲ ባለስልጣናት ቢገልጹም፣ የተገኘበት መረጃ ትክክለኛ በመሆኑ ውሳኔው የመቀልበስ እድሉ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ዴይሊ ስታር አስነብቧል፡፡