ስለተጠባቂው የሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታ አሃዞች ምን ይላሉ?
የአንፊልዱ ፍልሚያ በአየር ሁኔታ ምክንያት ሊራዘም ይችላል ቢባልም ሁለት ስብሰባዎች ተካሂደው ጨዋታው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ ተወስኗል
ቀያዮቹ ከቀያይ ሰይጣኖች ጋር ካደረጓቸው ያለፉት 13 ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንዱ ብቻ ነው
በ20ኛው ሳምንት ተጠባቂ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መሪው ሊቨርፑል በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ማንቸስተር ዩናይትድ ያስተናግዳል።
ምሽት 1 ስአት ከ30 የሚደረገው ጨዋታ የሰሜን ምዕራብ የእንግሊዝ ከተሞች በበረዶ መሸፈንን ተከትሎ ሊራዘም እንደሚችል ቢገመትም ሁለት የደህንነት ስብሰባዎች ተካሂደው ጨዋታው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ ተወስኗል።
የአየር ሁኔታው የማንቸስተር እና ሊቨርፑል አውሮፕላን ማረፊያዎችን ዛሬ ጠዋት እንዲዘጉ ያደረገ ቢሆንም ደጋፊዎች አንፊልድ ቢገኙ ጉዳት እንደማያደርስ ታምኖበት ውሳኔው መተላለፉን ፕሪሚየር ሊጉ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
በታህሳስ ወር መጀመሪያ ያጋጠመው "ዳራግህ" የተሰኘ ማዕበል ሊቨርፑል ከኤቨርተን ጋር ሊያደርገው የነበረውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ሊቨርፑል መሪነቱን ለማጠናከር፤ ዩናይትድ ከውጤት ቀውስ ለመውጣት
የዛሬ ምሽቱ የአንፊልድ ፍልሚያ የሊጉን መሪ ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር ያለውን የአምስት ነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ለማስፋት የሚያደርገው ነው።
በ23 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከወራጅ ቀጠናው ለመሸሽ ይጫወታል።
አሃዞች በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል የምሽቱን ጨዋታ እንደሚያሸነፍ ሰፊ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርጉ ናቸው።
ቀያዮቹ ከቀያይ ሰይጣኖቹ ጋር ካደረጓቸው ያለፉት 13 ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንዱ ብቻ ነው፤ ሰባት ጊዜ አሸንፈው በአምስቱ አቻ ተለያይተዋል።
የሮበን አሞሪሙ ዩናይትድ በአንፊልድ ካደረጋቸው ያለፉት ስምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ አላሸነፈም፤ በአራቱ ተሸንፎ በቀሪዎቹ ነጥብ ተጋርቷል።
በአንፊልድ ለማንቸስተር ዩናይትድ የመጨረሻዋን ጎል ያስቆጠረው (በ2018) ጀሴ ሊንጋርድ ነው።
ሞሀመድ ሳላህ በበኩሉ ከየትኛውም ጨዋታ በበለጠ ከዩናይትድ ጋር የሚደረገውን ይፈልገዋል። ሞ ሳላህ በፕሪሚየር ሊጉ ከ2020 ወዲህ በቀያይ ሰይጣኖቹ ላይ 12 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ከዩናይትድ ጋር በተደረጉ ግጥሚያዎች ከፍተኛውን ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበልም ቀዳሚ ነው፤ ሳላህ ስድስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሮበን አሞሪም ዩናይትድ ማሰልጠን ከጀመረ ወዲህ በፕሪሚየር ሊጉ ማሸነፍ የቻለው ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው። በቅርቡ በወልቭስ እና ኒውካስትል የደረሰበት ሽንፈትም ጫናው እንዲበረታበት አድርጓል።
በአንጻሩ ቀያዮቹን ከጀርመናዊው የርገን ክሎፕ የተረከቡት አርኔ ስሎት በዘንድሮው የውድድር አመት አንድ ጨዋታ ብቻ ነው የተሸነፉት። ከ18 ጨዋታዎች 45 ነጥብ በመሰብሰብ 20ኛውን የሊግ ዋንጫ ወደ አንፊልድ ለመውሰድ ስኬታማ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ።