ስለ አንፊልድ የሊጉ ተጠባቂ ጨዋታ አሃዞች ምን ይናገራሉ?
ባለፉት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ድል የራቃቸው ቀያዮቹ በ30ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃግብር መድፈኞቹን ይገጥማሉ
የየርገን ክሎፕ ቡድን ሊቨርፑል ባለፉት ስድስት የአንፊልድ ጨዋታዎች አርሰናልን ማሸነፍ ችሏል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ አርሰናል ወደ አንፊልድ አምርቶ ሊቨርፑልን ይገጥማል።
በ72 ነጥብ ፕሪሚየር ሊጉን እየመሩ የሚገኙት አምድፈኞቹ፥ በ29 ነጥብ ዝቅ ብለው 8ኛ ደረጃን ከያዙት ቀያዮቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ 12 ስአት ከ30 ላይ ይደረጋል።
ለተጠባቂው ጨዋታ በአርሰናል በኩል ቡካዮ ሳካ ከጉዳት መመለሱ የተነገረ ሲሆን፥ ቨርጂል ቫንዳይክም ከጉዳት አገግሞ ለቀያዮቹ እንደሚሰለፍ ተገልጿል።
የ2022/23 የውድድር አመት የሁለቱን ቡድኖች የነጥብ ልዩነት ቢያሰፋውም በታሪክ ሊቨርፑል በአርሰናል ላይ የበላይነት አለው።
ቀያዮቹ እና መድፈኞቹ ባለፉት ስድስት የአንፊልድ ግጥሚያዎቻቸው ባለሜዳው ክለብ አሸናፊ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
አርሰናል ከሜዳው ውጭ ከሊቨርፑል ጋር ባደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መሸነፉም የዛሬውን ጨዋታ ይበልጥ ተጠባቂ ያደርገዋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ሆኖ ከሊቨርፑል ጋር ባደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች በሶስቱ ያሸነፈ ሲሆን፥ ሁለቱን ሊቨርፑል አሸንፏል።
የመርሲሳይዱ ክለብ በታሪክ የተሻለ የበላይነት ቢይዝም በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ደካማ አቋም እያሳየ ነው የሚገኘው።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ድል የራቃቸው ቀያዮቹ፥ በሁለቱ ምንም ግብ አላስቆጠሩም። በአንፊልድ ግን ካለፉት ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች በአምስቱ አሽንፈው በአንዱ አቻ ወጥተዋል።
በታህሳስ ወር 2022 በሌስተር ከተቆጠረባቸው ጎል ወዲህ በአንፊልድ ምንም ጎል አልተቆጠረባቸውም።
ይህም አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ለሰባት ተከታታይ ጊዜ በሜዳቸው አርሰናልን በማሸነፍ ከያዙት ክብረወሰን ጋር ተዳምሮ የሊጉን መሪ ፈተና ያበዛዋል።
በመጀመሪያው ዙር የሊጉ ግጥሚያ በኤምሬትስ 3 ለ 2 ያሸነፉት መድፈኞቹ በ29 ነጥብ የራቁትን ሊቨርፑል በአንፊልድ አሸንፈው ከ2005 ወዲህ ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸንፉ ይሆን ወይ የሚለው በርካቶች እያነሱት ያለው ጥያቄ ነው።
በዚህ አመት ከሜዳው ውጭ ያደረገውን 14 ጨዋታ በማሸነፍ ከሊጉ ክለቦች ቀዳሚው የሆነው አርሰናል የአንፊልድ ያለፈ ታሪኩን ይቀይረዋል ብለው ይገምታሉ? ግምትዎን ያጋሩን