የየርገን ክሎፕ ቡድን በዚህ ፍልሚያ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቶታል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ የሊጉን መሪ አርሰናል ከሊቨርፑል በአንፊልድ ያገናኛል።
ምሽት 2 ስአት ከ30 የሚካሄደው ጨዋታ መድፈኞቹ መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት አልያም ቀያዮቹ ወደ መሪነት የሚመጡበት ስለሆነ እጅጉን ይጠበቃል።
ብራይተንን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሊጉን በ39 ነጥብ የሚመራው የሚኬል አርቴታ ቡድን በአንፊልድ ማሸነፍ አልያም አቻ መለያየት መሪነቱን ያጠናክርለታል።
ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር በአንፊልድ ነጥብ ከተጋራ በኋላ መድፈኞቹን የሚገጥመው የየርገን ክሎፕ ስብስብ በ38 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ እንደመቀመጡ የዛሬውን ፍልሚያ ካሸነፈ ነጥቡን 41 በማድረስ ሊጉን መምራት ይጀምራል።
የፕሪሚየር ሊጉ ኮምፒውተርም ቀያዮቹ የተሻለ የማሸነፍ እድል እንዳላቸው ግምቱን አስቀምጧል።
የቤትቪኮር ልዩ ኮምፒውተር ለመርሲሳይዱ ክለብ 47 በመቶ የማሸነፍ ግምት ሲሰጥ ለሰሜን ለንደኑ ክለብ 30 በመቶ ሰጥቷል።
በአንፊልድ የወትሮው ድባብ እየደበዘዘ መምጣቱ ያሳሰባቸው የርገን ክሎፕ በምሽቱ ጨዋታ አንድም ደጋፊ እንዳይቀር ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
የኮምፒውተሩን ግምት የሚያጣጥሉ የአርሰናል ደጋፊዎችና የቀድሞ ተጫዋቾች ግን አንፊልድ ለተቀናቃኝ ቡድን አስፈሪ መሆኑን ባይዘነጉትም ድል በማድረግ መሪነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ያምናሉ።
አርሰናልና ሊቨርፑል ከፈረንጆቹ 1995 ወዲህ 67 ጊዜ የተጋጠሙ ሲሆን ሊቨርፑል 24 ጊዜ አርሰናል ደግሞ 19 ጊዜ አሸንፈዋል፤ ቀሪዎቹን 24 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታዎች የሚገምተው ልዩ ኮምፒውተር በ68ኛው የሊቨርፑልና አርሰናል ፍልሚያ ቀያዮቹ የማሸነፍ እድላቸው ከፍ ያለ ነው ብሏል፤ የእርሶስ?