ፕሪሚየር ሊጉን ለመምራት በአንፊልድ የሚደረገው ፍልሚያ የቀያዮቹን የበላይነት ያስቀጥላል?
ሊቨርፑል በአንፊልድ ማንቸስተር ሲቲን ባስተናገደባቸው ያለፉት 20 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፈው
በማንቸስተር ሲቲ ላይ 11 ጎሎችን ያስቆጠረው ሞሀመድ ሳላህ ከጉዳት ተመልሷል
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ሊቨርፑልን ከማንቸስተር ሲቲ ያገናኛል።
ምሽት 12 ስአት 45 በአንፊልድ የሚደረገው ጨዋታ የሊጉን መሪነት ለመያዝ ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት ነው።
ትናንት በኤምሬትስ ብሬንትፎርድን 2 ለ 1 ያሸነፈው አርሰናል በ64 ነጥብ ሊጉን መምራት መጀመሩን ተከትሎ መድፈኞቹ የአንፊልዱ ፍልሚያ በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ ይጠባበቃሉ።
በአንፊልድ ለታላላቆቹ ክለቦች ጭምር የማይረታው ሊቨርፑል የፔፕ ጋርዲዮላውን ማንቸስተር ሲቲ በማሸነፍ ዳግም ወደ መሪነቱ ለመመለስ ይጫወታል።
ግብጻዊው ሞሀመድ ሳላህም ከጉዳት ተመልሶ በአንፊልዱ ፍልሚያ የፊት መስመሩን ይመራል ተብሏል።
በማንቸስተር ሲቲ በኩል ጀርሚ ዶኩ እና ማቲያስ ኑኔስ ለጨዋታው የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው የተባለ ሲሆን፥ ከዩናይትድ ጋር በነበረው የደርቢ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ፊል ፎደን አገግሞ ወደሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ አሃዛዊ መረጃዎች
- ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በአንፊልድ ባደረጋቸው ያለፉት 20 ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው፤ 13 ጊዜ አሸንፎ በስድስቱ አቻ ተለያይቷል
- ቀያዮቹ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ሲቲን ያሸነፉት ግን አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ባለፈው የውድድር አመት 1 ለ 0 በሆነ ውጤት
- ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 153 ጊዜ ተገናኝተው ቀያዮቹ 93 ጊዜ አሸንፈዋል፤ ዘ ሲቲዝንስ ደግሞ 50 ጊዜ ረተዋል
ሊቨርፑል
- ቀያዮቹ ባለፉት ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ስምንቱን (በየካቲት ወር በአርሰናል ከደረሰባቸው የ3 ለ 1 ሽንፈት ውጭ) አሸንፈዋል
- የየርገን ክሎፕ ቡድን ከመመራት ተነስቶ 22 ነጥቦችን በመስብሰብ ሲቲን በአንድ ነጥብ ይበልጣል
- የሊቨርፑል 10 የፕሪሚየር ሊግ ጎሎች በጭማሪ ስአት የተቆጠሩ ናቸው
- ሞሀመድ ሳላህ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በተደረጉ ግጥሚያዎች 19 ጊዜ ተሰልፎ 11 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ ሰባት ጎል የሆኑ ኳሶችንም አቀብሏል
- ዳርዊን ኑኔዝ ባለፉት 10 ጨዋታዎች (ሁሉም ውድድሮች) ስምንት ጎሎችን አስቆጥሯል
ማንቸስተር ሲቲ
- የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በሁሉም ውድድሮች ከሜዳው ውጭ 10 ጨዋታዎችን በተከታታይ ለማሸነፍ ወደ አንፊልድ አቅንቷል፤ ዛሬ ይህን ካሳካ ለጋርዲዮላ ሶስተኛው ስኬታቸው ይሆናል
- ባለፉት 12 የሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፉም፤ በ10 አሸንፈው በሁለቱ ነጥብ ተጋርተዋል
- ፊል ፎደን በዚህ የውድድር አመት በሁሉም ውድድሮች 18 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ በፕሪሚየር ሊጉም በ18 ጎሎች ላይ ተሳትፎ አድርጓል
- ሃላንድ ሲቲ ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው ያለፉት ሶስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ጎል አላስቆጠረም
- ሲቲ በዚህ የውድድር አመት ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው ጨዋታዎች 25 ጎሎችን አስቆጥሯል፤ 10 ተቆጥሮበታል
- በአስቶን ቪላ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ከደረሰባቸው የ1 ለ 0 ሽንፈት ውጭ ባለፉት 20 ጨዋታዎች (በሁሉም ውድድሮች) ጎል አስቆጥረዋል
ጋርዲዮላ ከክሎፕ
- ጀርመናዊው የቀያዮቹ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ከየትኛውም አሰልጣኝ በበለጠ (29 ጊዜ) ከስፔናዊው ፔፕ ጋርዲዮላ ጋር ተፋልመዋል
- ክሎፕ ሊቨርፑልን እያሰለጠኑ 21 ጊዜ ከጋርዲዮላ ጋር ተገናኝተው በስምንቱ አሸንፈው፤ በሰባቱ ሽንፈት ገጥሟቸዋል