በቦረና ዞን ተልታሌ ወረዳ የአንበጣ መንጋ መከሰቱ ተገለፀ
የአንበጣ መንጋው በ400 ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ዞኑ አስታውቋል
አንበጣው እየደረሱ ባሉ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ድጋፍ ተጠይቋል
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልታሌ ወረዳ በሚገኙ 5 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአንበጣ መንጋው በወረዳው በሚገኙ መካሳ፣ ጋዲል፣ ኤል ኩኔ እና ዋንዶ ዲግሬ በተባሉ 5 ቀበሌዎች መከሰቱን በተልታሌ ወረዳ የግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የቁጥጥር እና ክትትል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ እንግዳ ዮሃስ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም የአንበጣ መንጋው በ400 ሄክታር መሬት ላይ በማረፍ ጉዳት ማስከተሉን እና ከዚህም ውስጥ 30 ሄክታር መሬት ላይ የኬሚካል ርጭት መደረጉ የተልታሌ ወረዳ የግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮኃላፊ አቶ በርሃኔ አማረ ገልጸዋል።
የኬሚካል ርጭቱን ስራ በመኪና በማከናወን ላይ መሆኑን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ይህም ስራውን በሚፈለገው ፍጥነት ለማከናወን አዳጋች እንዳደረገው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው የአውሮፕላን ርጭት አሁን ላይ አለመኖሩን ያስታወቁት አቶ ብርሃኔ፤ አንበጣው እየደረሱ ባሉ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የግብርና ሚኒስቴር፤ በኢትዮጵያ አንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ማስታወቁ ይታወሳል።
በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋትጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ በወቅቱ ለአል ዐይን አማረኛ እንደተናገሩት፥ አሁን ላይ ከበረሃ አንበጣ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ ነው ብለው ነበረ።
በፑንትላንድ እና ቀይ ባህር አካባቢ መጠነኛ መራባቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ በላይነህ፤ ሚኒስቴሩ ካለው ዝግጁነትና ኃይል ጋር ሲነጻጸር መቆጣጠር የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለው መግለጻቸውም ይታወሳል።
ሀገር ውስጥም ቢሆን ዝናብ ቢጥል እና የመራባት አቅም ቢኖረውም ሚኒስቴሩ ካለው አቅም አንጻር “በቂ ዝግጅት ስለተደረገ መቆጣጠር ይቻላል” ብለዋል።