በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል የአንበጣ መከላከያ የአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት ማካሄድ አልተቻለም- ግብርና ሚኒስትር
በአፋር እና በሶማሌ ክልል ሁለት ዞኖች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
ከአንበጣ በተጨማሪ ግሪሳ ወፍ ሌላኛው የሰብል ውድመት ስጋት መደቀኑ ተነግሯል
የአንበጣ መንጋ በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል ሁለት ዞኖች መከሰቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ብዙዎችን ለእርዳታ ሲዳርግ ቆይቷል።
መንጋውን የፌደራል መንግስት ክልሎችን እና ሌሎች በምግብ ዋስትና ላይ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተደረገ ድጋፍ ጉዳቱን መቀነስ እንደተቻለ ሲገለጽ ይሰማል።
አሁን ላይ ደግሞ የአንበጣ መንጋው በአፋር እና በሶማሊ ክልሎች መከሰቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
- በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የአንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ
- የአንበጣ መንጋ ክስተት በኢትዮጵያ ለተወሰኑ ጊዜያት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ትንበያዎች አመለከቱ
በሚኒስቴሩ የዕፀዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት የአንበጣ መንጋው በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል ሲቲ እና ፋፈን ዞኖች ተከስቷል ብለዋል።
በሶማሌ ክልል ሁለቱ ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በሶማሊ ላንድ በኩል አድርጎ የገባ ሲሆን፤ አሁን ላይ የኬሚካል ርጭት በአውሮፕላን በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በአፋር ክልል ባሉ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በኩብኩባ ደረጃ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ በላይነህ፤ መንጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከምስራቅ አማራ ወረዳዎች ጋር የሚዋሰኑ በመሆኑ መንጋው የመዛመት አድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
መንጋው የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ እና እንዳይዛመት በሰው ሀይል እና በመኪና የኬሚካል ርጭት የፌደራል መንግስት ከአፋር ክልል መንግስት ጋር በመቀናጀት በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አቶ በላይነህ ገልጸዋል።
መንጋው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቀላሉ ለመቆጣጠር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ማካሄድ ቢያስፈልግም በአካባቢው ጦርነት መኖሩ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።
የአውሮፕላን ርጭት ለማካሄድ አውሮፕላኑ የግድ ዝቅ ብሎ መብረር አለበት የሚሉት አቶ በላይነህ ይሄንን ለማድረግ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከኢትዮጵያ አየር ሀይል እና ከሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።
ይሁንና ዘንድሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እና በቀላሉ በቁጥጥር ሰር ማዋል እንደሚቻል አቶ በላይነህ ነግረውናል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሰብል ልማት ስራው ላይ ከአንበጣ መንጋው በተጨማሪ የግሪሳ ወፍ ሌላኛው ስጋት መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የግሪሳ ወፍ የስምጥ ሸለቆን ተከትሎ በመንጋ የሚንቀሳቀስ ሰብል አውዳሚ የወፍ ዝርያ ሲሆን፤ ርጭቱን ለማከናወን የአውሮፕላን እና የኬሚካል ዝግጅቱ መጠናቀቁም ተገልጿል።