የለንደን ከንቲባ ሳዲቅ ካሀን ከቴይለር ስዊፍት የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ የሙስና ምርመራ ተጀመረባቸው
ከንቲባው የ3 ሺህ ፓውንድ ቲኬት በስጦታ ተቀብለዋል ተብሏል
የከተማዋ ፖሊስ የቴይለር ስዊፍትን ኮንሰርት ለመጠበቅ ያወጣው የ500 ሺህ ፓውንድ ወጪ የተጋነነ ነው የሚል ትችቶች ቀርቦበታል
የለንደን ከንቲባ ሳዲቅ ካሀን ከቴይለር ስዊፍት የሙዚቃ ኮንሰርት ጋር በተያያዘ የሙስና ምርመራ ተጀመረባቸው።
አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ቴይለር ስዊፍት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት በአውሮፓ ሀገራት ከተሞች በርካታ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን አድርጋለች።
ኮንሰርቱ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል ለንደን አንዷ ስትሆን የከተማዋ ከንቲባ ሳዲቅ ካሀን ደግሞ ሶስት ሺህ ፓውንድ ዋጋ ያላቸው የኮንሰርት መግቢያ ቲኬቶችን በስጦታ ተቀብለዋል ተብሏል።
ከንቲባው ባልተገባ መልኩ ከቴይለር ስዊፍት ስጦታ መቀበላቸው ሙስና ነው በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የለንደን ከንቲባ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከኮንሰርቱ ቲኬት ጋር በተያያዘ የአስተዳድር ስህተት እንደነበር እና ስህተቱ ወዲያው እንደታረመ ለዴይሊ ሜይል ተናግረዋል።
ቴይለር ስዊፍት በዊምብሌይ ስታዲየም ባደረገችው ተከታታይ የሙዚቃ ኮንሰርት የሀገሪቱ መንግሥት ለአንድ ምሽት 99 ሺህ ፓውንድ በድምሩ 500 ሺህ ፓውንድ ገደማ ወጪ አድርጓል።
ለኮንሰርቱ የደህንነት ጥበቃ ወጪ ተደርጓል የተባለው ገንዘብ በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች ከተካሄዱት ተመሳሳይ ኮንሰርቶች ጋር ሲነጻጸር በትንሹ የ30 ሺህ ፓውንድ ብልጫ አሳይቷል ተብሏል።
ይህ መሆኑ ቴይለር ስዊፍት ለሳዲቅ ካሀን ሰጥተዋለች ከተባለው የኮንሰርት መግቢያ ቲኬት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል እየተገለጸ ይገኛል።
ይሁንና የከተማዋ ፖሊስ ወጪው የጨመረው ቴይለር ስዊፍት በኦስትሪያ ቬና ልታካሂደው የነበረው ኮንሰርት በሽብር ጥቃት ስጋት ምክንያት በመራዘሙ እና ተጨማሪ ጥበቃ ማድረግ በማስፈለጉ እንደሆነ ተገልጿል።