ባለፉት ሁለት አመታት በመላው ብሪታንያ የተሰረቁ የሞባይል ስልኮች ከ48 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ያወጣሉ
በብሪታንያዋ ዋና ከተማ ለንደን የሞባይል ስርቆት ተባብሶ መቀጠሉ ተሰማ፡፡ በየስድስት ደቂቃው አንድ ስልክ በሚመነተፍባት ለንደን ፖሊስ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ስራ በዝቶበታል ተብሏል፡፡
ስርቆቱን የሚፈጽሙት ግለሰቦች በሞተር ሳይክል እና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ከሰዎች ላይ ሞባይሎችን መንትፈው እንደሚሰወሩ ነው የተነገረው፡፡
በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በከተማዋ ከፍተኛ የሞባይል ስርቆት መስፋፋቱን ያስታወቀው ፖሊስ በ2022፣ 92 ሺህ በ2023 ደግሞ 52 ሺህ ስልኮች መሰረቃቸውን አስታውቋል፡
ስርቆቱ በሰፊው የሚታየባቸው ቱሪስቶች ይበዙባቸዋል በሚባሉት ዌስትሚንስተር (25ሺህ) ፣ ካምደን (7892) ፣ ሳውዝዋርክ (5892) እና ኒውሀም(4616) ስልኮች ተሰርቀዋል ፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ ከ40-50 የሞባይል ስርቆት ሪፖርቶች የሚደርሱት የለንደን ፖሊስ ሞባይሎችን ለማስመለስ በሚያድርገው ጥረት አብዘሀኞቹ ውጤታማ አይደሉም፤ እስካሁን ስርቆት ከተፈጸመባቸው ሰዎች ስልኮቻቸው የተመለሰላቸው ሁለት በመቶ ብቻ ናቸው፡፡
ስልኮቹ ከተሰረቁ በኋላ በፍጥነት መረጃቸው ተሰርዞ ለሶስተኛ ወገን መሸጣቸው የፖሊስን ክትትል አደጋች ማድረጉ ነው የተነገረው፡፡
የሞባይል ስርቆት ጎብኝዎች እና ዜጎች ደህንነት እንዳይሰማቸው የሚያደርግ ከፍተኛ ወንጀል ነው ያለው የከተማዋ ፖሊስ፤ በርካታ ስርቆት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች የሚሰማሩ ፖሊሶችን ቁጥር በመጨመር ወንጀሉን ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ ይህን ቢልም ነዋሪዎች ከስርቆቱ በኃላ ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ቢያደርጉም ፖሊስ ምንም ማድረግ የማይችል ስለመሆኑ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሁለት አመታት በመላው ብሪታንያ የተሰረቁ የሞባይል ስልኮች ከ48 ሚሊየን ፓውንድ በላይ እንደሚወጡ ደይሊ ሜል አስነብቧል፡፡
በ2022 በአለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ 374 ስልኮች በተለያዩ መንገዶች የተሰረቁ ሲሆን በዚሁ አመት ከ499 ሰዎች መካከል የአንድ ሰው ስልክ ተሰርቋል፡፡