ከሰሞኑ በአዲስ አበባ እየታዩ የሚገኙት ረጃጅም የነዳጅ ሰልፎች መነሻ ምንድን ነው?
ከሀሙስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ረጃጅም የነዳጅ ሰልፎች መኖራቸውን አል ዐይን አማርኛ ቅኝት ባደረገባቸው ስፍራዎች ታዝቧል
የከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የፈረሱ የነዳጅ ማደያዎች ለሰልፎቹ መብዛት አንድ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል
ከሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጀምሮ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ተሸከርካሪዎች የፈጠሯቸው ረጃጅም ሰልፎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡
ከሀሙስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ረጃጅም የነዳጅ ሰልፎች መኖራቸውን አል ዐይን አማርኛ ቅኝት ባደረገባቸው ስፍራዎች ታዝቧል፡፡
ቅኝት ካደረግንባቸው አካባቢዎች መካከል መገናኛ ፣ አራት ኪሎ ፣ ካዛንችስ እና ሰሚት አካባቢዎች ረጃጅም ሰልፎች የሚስተዋልባቸው ሲሆን በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ ነዳጅ የለም የሚሉ ምልክቶችን ተመልክተናል፡፡
አራት ኪሎ አካባቢ ሰልፍ ተሰልፈው ካገኝናቸው አሸከርካሪዎች መካከል የታክሲ ሾፌር የሆነው ኤፍሬም ታደሰ እንደሚለው፤ “ነዳጅ ሲራገፍ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ለሰአታት በሰልፍ ላይ ቆመን ካሳለፍን በኋላ ነዳጅ አልቋል ይሉሀል። ከእዚያ ደግሞ ሌላ ቦታ ሂደህ ረጅም ሰልፍ ለመጠበቅ ትገደዳለህ፤ በዚህ የተነሳም ከሀሙስ እና አርብ ጀምሮ በተገቢው መንገድ ስራ እየሰራን አይደለም” ብሏል፡፡
ስራ ፈተን ነዳጅ ፍለጋ መሽከርከር ከጀመርን አራት ቀን አልፎናል የሚለው ሌላኛው የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ አቤል ገበየሁ በበኩሉ “አሁን ከሚገኝው የነዳጅ ዋጋ አንጻር እንደድሮው በርከት አድርገን ነዳጅ አንቀዳም። ለአንድ እና ለሁለት ቀን የሚያሰራንን ብቻ ነው የምንገዛው፤ በዚህ የተነሳም እንደዚህ አይነት ለተከታታይ ቀናት የነዳጅ እጥረት ሲፈጠር ስራ ፈተን በመቀመጣችን የሚደርስብን ኢኮኖሚያዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም” ሲል ቅሬታውን ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ በሚገኙ 120 የነዳጅ ማደያዎች በቀን 1.6 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ እያቀረበ እንደሚገኝ የሚናገረው የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እየታየ በሚገኝው ልክ ረጃጅም ሰልፎችን ሊፈጥር የሚችል የነዳጅ እጥረት የለብኝም ብሏል፡፡
በባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር በቀለች ኩማ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት መስርያ ቤታቸው ረጃጅም ሰልፎቹ ለምን እንደተፈጠሩ ባለሙያዎችን መድቦ ባደረገው ዳሰሳ የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ረጃጅም ሰልፎችን በመመልከት "ነዳጅ ጠፍቷል" በሚል የሚሰለፉ ተሸከርካሪዎች የፈጠሩት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው አጠቃላይ ነዳጅ አዲስ አበባ ከተማ 42 በመቶውን ድርሻ እንደምትወስድ የሚናገሩት የኮሚኒኬሽን ሀላፊዋ በተለምዶ በቀን 1.4 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ለመዲናዋ እንደሚሰራጭ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ እስከ 1.7 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ድረስ እየተከፋፈለ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በቀን ከሚያስፈልገው ፍጆታ ያነሰ የነዳጅ አቅርቦት በገበያ ውስጥ የለም ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በየማደያዎቹ የሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማሽኖች አገልግሎት አለመስጠታቸው ለሰልፉ መበርከት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
“አሽከርካሪዎች የነዳጅ አቅርቦት ችግር በመዲናዋ ባለመኖሩ ረጃጅም ሰልፎች ላይ በመሰልፍ ጊዜያቸውን ከሚያባክኑ ይልቅ በሌሎች አካባቢዎችም ቅኝት በሚያደርጉ ተመራጭ ነው” ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እያካሄደ በሚገኝው የኮሪደር ልማት የፈረሱ ማደያዎች ለሰልፎቹ መብዛት እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር እስካሁን በተካሄደው የኮሪደር ልማት ስምንት ማደያዎች መፍረሳቸውን ገልጸው አራዳ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ብዙ ማደያዎች ከፈረሱባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
“በኮሪደር ልማቱ በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ የፈረሱ ማደያዎች አሉ፤ ሙሉ ለሙሉ የፈረሰባቸውን ማደያዎች ጥናት ተጠንቶ ተቀያሪ ቦታ እንዲሰጣቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በኮሪደር ልማቱ ምን ያህል ማደያዎች ሊፈርሱ እንደሚችሉ እንዲሁም ተጨማሪ ማደያዎችን ለመገንባት ባለስልጣኑ እቅድ ስለመያዙ የጠየቅናቸው ዳይሬክተሯ ፤
“ነዳጅ ማደያ በተገኝበት ቦታ አይገነባም፤ በየክፍለ ከተማዎቹ ያለው የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ተጠንቶ በረጅም ርቀት ልዩነት ውስጥ ማደያ የሌለባቸው ስፍራዎች ካሉ በእነርሱ ላይ ፈቃድ የሚሰጥ ይሀናል። አሁን ባለው ግምገማ ግን በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት 120 ማደያዎች በቂ ናቸው ብለን እናምናለን” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
እስከ ትላንት ማክሰኞ ድረስ 5.8 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ መራገፉን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል
ረጃጅም ሰልፎቹ በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ባለመፈጠሩ በቀጣይ በነዳጅ ማደያዎች አሰራር ጋር በተያያዘ ቀልጣፋ አገልግሎት መሰጠት እንዲቻል ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡