የአሜሪካዋ ሊውዚኒያ ግዛት አስርቱ ትዕዛዛት በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲለጠፉ አዘዘች
ሪፐብሊካኖች በሚመሯቸው ቴክሳስ፣ ኦክላሆማ እና ኡታህም ተመሳሳይ ህግ ለማውጣት ታቅዷል
በ1980 ኬንታኪ መሰል ህግ አውጥታ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት የሃይማኖትና መንግስትን መለያየት ይቃረናል በሚል ውድቅ አድርጎት ነበር
የአሜሪካዋ ሊውዚኒያ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ በማዘዝ የመጀመሪያዋ ግዛት ሆናለች።
በሪፐብሊካኖች ድጋፍ የተሰጠውን ውሳኔ ህግ አድርገው የፈረሙት የግዛቷ አስተዳዳሪ ጄፍ ላንድሪ አስርቱ ትዕዛዛት “የሀገራችን እና የመንግስት መሰረት ናቸው” ብለዋል።
ግዛቷ ያጸደቀችው ህግ አስርቱ ትዕዛዛት ጎላ ብለውና በቀላሉ እንዲነበቡ ተደርገው እንዲጻፉ የሚያዝ ሲሆን፥ የሚጻፉበት ፖስተር መጠንም ወርዱ 28 ሴንቲሜትር ቁመቱ ደግሞ 35.5 ሴንቲሜትር እንዲሆን ያዛል።
እያንዳንዱ ትዕዛዛት በአሜሪካ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ወሳኝ ድርሻ እንደነበራቸው የሚገልጡ አጫጭር ማብራሪያዎች እንዲኖራቸው ነው ህጉ ያስቀመጠው።
በአሜርካ መንግስት ድጋፍ በሚደረግላቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ ከ2025 ጀመሮ በሁሉም የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት የተጻፉባቸው ፖስተሮች እንዲለጠፉ ተወስኗል።
ሪፐብሊካኖች በሚመሯቸው ቴክሳስ፣ ኦክላሆማ እና ኡታህም ተመሳሳይ ህግ ለማውጣት በቅርቡ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
“አትስረቅ፣ አታመንዝር፣ አትግደል” የሚሉት አስርቱ ትዕዛዛት አብዛኞቹ በሁሉም እምነቶች ተቀባይነት ቢኖራቸውም የተወሰኑት ከክርስትና እምነት ጋር ብቻ የተያያዙ ናቸው።
ይህም ትዕዛዛቱን በአሜሪካ በትምህርት ቤቶች፣ በችሎት አዳራሾች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ለመለጠፍ የሚደረጉ ጥረቶች ወደ ፍርድቤት እንዲያመሩ ማድረጉ ነው የሚነገረው።
ኬንታኪ በ1980 በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መማሪያ ክፍሎች ውስጥ አስርቱ ትዕዛዛት እንዲለጠፉ ያሳለፈችው ውሳኔ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድቤት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ከትዕዛዛቱ ውስጥ “ከእግዚያብሄር ውጭ አታምልኩ” እና “ሰንበትን አክብሩ” የሚሉ በግልጽ ሃይማኖታዊ የሆኑ ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቀሰው ፍርድቤቱ፥ የኬንታኪ ውሳኔ “ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ነው” በሚል ነበር ውድቅ ያደረገው።
የሊውዚኒያ ግዛት ትናንት ያሳለፈው ውሳኔም የአሜሪካ ህገመንግስት ያስቀመጠውን የሃይማኖትና መንግስት መለያየት ይቃረናል በሚሉ የሲቪል መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ እንደሚገጥመው ይጠበቃል።