ሉፍታንዛ አየር መንገድ ወደ ቴህራን የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ
አየር መንገዱ በረራውን ያቋረጠው ኢራን በእስራኤል ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች በሚል ነው
ከኢራን በተጨማሪም አየር መንገዱ ወደ አረብ ሀገራት ያለውን በረራ አቋርጧል
ሉፍታንዛ አየር መንገድ ወደ ቴህራን የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ፡፡
የጀርመኑ ሉፍታንዛ አየር መንገድ ከአውሮፓ ወደ ኢራን መዲና ቴህራን ከሚበሩ ጥቂት የአውሮፓ አየር መንገዶች መካከል ዋነኛው ሲሆን ለጊዜው በረራውን ማቋረጡን አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ለሁለት ቀናት ወደ ቴህራን የሚያደርገውን በረራ ማቆሙን ያስታወቀ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ኢራን በእስራኤል ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች በሚል እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ እስራኤል በሶሪያ መዲና ደማስቆ ከተማ ባለው ኢምባሲዋ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ሁለት ጀነራሎቿን ጨምሮ ዘጠኝ የኢራን ዜጎቿ ባሳለፍነው ሳምንት ለተፈጸመባት ጥቃት የአጸፋ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ተገምቷል፡፡
የኢራን ጦር ወታደራዊ ዘመቻ ላይ እንደሆነ ማሳወቁን ተከትሎ የሉፍታንዛ አየር መንገድ መንገደኞች የጥቃቱ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል አየር መንገዱ ከአውሮፓ ከተሞች ወደ ቴህራን እንዲሁም ከቴህራን ወደ አውሮፓ ከተሞች ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችን ሰርዣለሁ ሲል አሳውቋል፡፡
በእስራኤል እና ኢራን መካከል የቀጥታ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት ያለ ሲሆን አሜሪካ ከእስራኤል ጎን እንደምትቆም አሳውቃለች፡፡
የኢራን ድሮን የሱዳኑን የእርስበእርስ ጦርነት ሁኔታ ይቀይረው ይሆን?
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ኳታር እና ኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ደውለው ኢራን ከእስራኤል ጋር ያላትን መካረር እንድትቀንስ እንዲያግባቡ መጠየቃቸውም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል በበኩሏ ከኢራን ምድር ወታደራዊ ጥቃት ከተሰነዘረባት ኢራንን በቀጥታ እንደምታጠቃ አስጠንቅቃለች፡፡
በርካታ ወታደራዊ ተንታኞች በበኩላቸው ኢራን በእስራኤል ላይ የቀጥታ ጥቃት ላትሰነዝር እንደምትችል ነገር ግን በኢራን የሚደገፉ የተለያዩ ታጣቂዎች እና ቡድኖች ግን እስራኤልን ሊያጠቁ እንደሚችሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡